ጠ/ሚ ዐቢይ በኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ያካፈሉት ተሞክሮ ኢትዮጵያ በለውጥ ተምሳሌትነት እንድትታይ ያስቻለ ነው – ቢልለኔ ስዩም

ቢልለኔ ስዩም

ኅዳር 18/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ያካፈሉት ተሞክሮ ኢትዮጵያ በለውጥ ተምሳሌትነት እንድትታይ ማስቻሉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቪየና-ኦስትሪያ ቆይታን በማስመልከት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቪየና-ኦስትሪያ ያደረጉት ቆይታ ሁለት አላማዎች እንዳሉት አንስተው ክብር እንግዳ ሆነው በመገኘት ቁልፍ መልእክት አስተላልፈዋል ብለዋል።

በዋነኝነት ደግሞ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያከናወነቻቸውን የለውጥ ስራዎችና ያገኘቻቸውን አመርቂ ውጤቶች በጉባኤው አካፍላለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባለፉት 5 ዓመታት በፖሊሲ ደረጃ ከፍተኛ ለውጦችን እያመጣች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማመልከታቸውንም ኃላፊዋ አንስተዋል።

በዚህም ተስማሚ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር፣ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማስተካከልና ተጨማሪ ማሻሻያዎችን በማከናወን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎች መቀየሷን ማመላከታቸውንም ገልጸዋል።

የሀገር በቀል የለውጥ አጀንዳ ዋና ምሰሶ በሆኑት ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ አይሲቲ፣ ማዕድንና ቱሪዝም በኩል የተከናወኑ ተግባራትንና ለውጦችን በጉባኤው ማካፈላቸውን አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉን በተመለከተ በአርንጓዴ ስልትና ፖሊሲ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ አተኩራ እየሰራች መሆኑን ማስገንዘባቸውንም አንስተዋል።

በስራ ፈጠራ ረገድ ዜጎች በሀገራቸው ልማት እንዲሳተፉና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲጠናከር እየተከናወኑ የሚገኙ ተጨባጭ ስራዎችን ማካፈላቸውንም ኃላፊዋ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ኢትዮጵያ ባለፉት 5 ዓመታት ያከናወነቻቸውን የለውጥ ስራዎች እንደ ተምሳሌትነት መጥቀሳቸውንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሶስት እጥፍ የምርት እድገት ማሳየቷንና ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተጨባጭ እርምጃ እንደሆነ መመስከራቸውን ገልጸዋል።

በኢንዱሰትሪው ዘርፍ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን እንደሚገባ በጉባኤው መነሳቱን ተናግረዋል።