ኢትዮ ቴሌኮም በጅግጅጋ ከተማ የ5ጂ አገልግሎት አስጀመረ

ሕዳር 18/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛው ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በጅግጅጋ ከተማ በይፋ አስጀመረ።

የ5ጂ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ዓለም የደረሰበት የመጨረሻው ፈጣኑ ገመድ አልባ የኔትወርክ አገልግሎት ሲሆን መረጃዎችን እጅግ በፈጠነ (በብርሃን ፍጥነት) ሁኔታ ለመለዋወጥ የሚያስችል ነው።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም ከመደበኛ አገልግሎት ባሻገር በርካታ አገልግሎቶች ለማህበረሰብ እያቀረበና የወቅቱን ቴክኖሎጂ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

በእለቱ በከተማው የተጀመረው የ5ኛው ትውልድ ኔትወርክ አገልግሎት በተለይም የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል እና የስራ እድልን በማፍጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮ ቴሌኮም ካሉት 73 ሚሊየን የሚጠጉ ደንበኞች መካከል የ5ጂ ተጠቃሚዎች ቁጥር 630 ሺሕ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም የተጠቃሚዎች ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው በከተማው የተጀመረው የ5ጂ አገልግሎት የነዋሪውን የዲጂታል ግብይት ስርዓት የሚያጠናክር መሆኑና ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም የቱሪዝምና የእንስሳት ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር የአምስተኛው ትውልድ የኔትወርክ አገልግሎት መጀመሩ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ (5G) አገልግሎት በሰከንድ ከ10 ጊጋ ባይት በላይ የሚደርስ ጥቅል መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የ5ጂ አገልግሎቱ በጅግጅጋ ከተማ በሚገኙ ሰባት ሳይቶች የተጀመረ ሲሆን በቅርቡም በአምስት ተጨማሪ አካባቢዎች ላይ ይጀመራል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ 5ጂን ካስጀመሩ 16 ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ የታወቃል፡፡

ተስፋዬ ኃየሉ (ከሐረር ቅርንጫፍ)