138 የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች ተላለፉ

ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 138 የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች አስተላለፉ።

በከተማዋ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን እና ሁሉም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ በቀጣይም መሰል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።

ምክትል ከንቲባዋ ኢትዮጵያ የሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፣ የውሃ ሙሌቱ እና ሀገራዊ ምርጫው በስኬት እንዲካሄድ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች በአንድነት መቆም እና መሰለፍ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሽታዬ መሀመድ በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ 117 የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች መሰጠቱን አውስተው፣ በዛሬው ዕለትም 138 በጠቅላላው ለ255 ነዋሪዎች የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ተሰጥተዋል ነው ያሉት፡፡

በዛሬ ዕለት ከተላለፉት ቤቶች አካል ጉዳተኞች፣ ለሀገር ባለውለታዎች፣ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ተጠቃሚ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡