ለአራተኛው ዙር ሀገራዊ የህዝብና ቤት ቆጠራ በደቡብ ክልል 29ሺ የሚጠጉ የቆጠራ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል

በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት  ዘንድሮ በመላ ሀገሪቱ የካቲት 4/2010 አራተኛው ዙር ብሄራዊ የህዝብና ቤት ቆጠራ በተመሳሳይ ወቅት እንደሚካሄድ ጠቁመዉ በክልሉ 29 ሺ የሚጠጉ የቆጠራ ቦታዎች መዘጋጀታቸዉን አመልክተዋል፡፡

የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሀይሉ እንዳሉት ለዚህ ስኬትም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን በምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራ የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽንም ተቋቁሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ በደቡብ ክልል ቀደም ሲል በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሃያ ስምንት ሺ ዘጠኝ መቶ አምሳ አራት የቆጠራ ቦታዎች ተመርጠው ዝግጁ ሆነዋል፡፡በእነዚህ የቆጠራ ቦታዎች ተመድበው የቆጠራ ስራውን የሚያከናውኑ 29ሺ ቆጣሪዎችና 7ሺ አንድ መቶ ተቆጣጣሪዎችም ተመልምለዋል፡፡ከዚሁ ጋር ተያይዞም የቆጠራ ቦታ ካርታ ዝግጅትና በሁለት ዙር የሙከራ ቆጠራ ጥናት የተካሄደ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው ከግብኣት፣ከቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተግባራትም በ35 የስልጠና ክልላዊ ማዕከላት በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

የዘንድሮው የህዝብና ቤት ቆጠራ ሙሉ በሙሉ በዲጅታል ቴክኒሎጂ የሚታገዝ በመሆኑ፣በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ወቅት የሚካሄድና ማስፈጸሚያ ሰነዶቹ በኦሮምኛ፣በአፋርኛ፣በሶማሊኛና በአማርኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በመሆናቸው ልዩ ያደርገዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ ግለሰቦችና ቤተሰቦች ሳይደገሙ ወይም ሳይታለፉ እንዲቆጠሩ የሚያስችል አሰራር እንደተዘረጋለትም አብራርተዋል፡፡

የቆጠራው ውጤት ተጨባጭ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎችን በማመላከት በድህነት ቅነሳ፣የተመጣጠነ እድገትን በማስፈን፣የህዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል፣የህዝቡን አሰፋፈርና ስርጭት በማመላከት፣ለምርምርና ጥናት በአጠቃላይም ፖሊሲዎችን ለመንደፍና አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አቶ ብርሃኑ ጠይቀዋል፡፡

ቆጠራው በወቅቱ ያለውን የአስተዳደር መዋቅር መሰረት ባደረገ መልኩ የሚካሄድ ሲሆን በየመዋቅሩ የትምህርትና ቅስቀሳ ኮሚቴዎች በመቋቋም የህዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡በቆጠራ ካርታ በወቅቱ አለመጠናቀቅ፣በግብኣት አቅርቦት መጓተትና በሌሎችም አንዳንድ ምክንያቶች ቀደም ሲል በህዳር ወር ሊካሄድ ከታሰበበት የጊዜ ሰሌዳ ወደ የካቲት 4/2010 መተላለፉንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡