በ32ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የአህጉሪቱን የለውጥ እንቅስቃሴ መገምገም ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በአፍሪካ ህብረት 32ኛው የመሪዎች ጉባኤ የህብረቱን የለውጥ እንቅስቃሴ ሪፖርት በዝርዝር መገምገም ቀዳሚ አጀንዳ እንደሚሆን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

“አስተማማኝ መፍትሄ በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚፈናቀሉ አፍሪካዊያን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች” በሚል መሪ ሃሳብ የህብረቱ አባል አገራት ዓመቱን ሙሉ ትኩረት አድርገው የሚሰሩበት አጀንዳ ይሆናል ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ15ኛ የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባና 32ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ 32ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በሚኒስትሮች ደረጃ ጥር 30 እና የካቲት 1 እንዲሁም በመሪዎች ደረጃ የካቲት 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል።

የህብረቱ ተቋማዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በወቅቱ የህብረቱ ሊቀ መንበርና የሩዋንዳ ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ እና በህብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህማት ይቀርባል።

የህብረቱ ዋና አጀንዳ የሆነው የለውጥ ተቋማዊ አደረጃጀትና እንቅስቃሴው ምን ደረጃ ላይ እንዳለም በዝርዝር ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የህብረቱ አባል አገራት ዓመቱን ሙሉ ትኩረት አድርገው የሚሰሩበትና ክትትል የሚደረግበት አጀንዳም ይመረጣል።

የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካውያንን እሴት በሚያንጸባርቅ መልኩ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አርቲስቶች የሚሳተፉበት የጋራ የሙዚቃ መርሃ ግብርም ይዘጋጃል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

የኢትዮጵያን ባህል፣  ወግ፣ እሴት የሚገልጽ አለባበስ የመርሃ ግብሩ አካል መሆኑን የገለጹት አቶ ነብያት፤ ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ መሆናቸውንም በተግባር የሚያሳዩበት ልዩ አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል፡፡ (ኢዜአ)