ትምህርታዊ ምርምሮችን ለሀገራዊ ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ተገለጸ

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ትምህርታዊ ምርምሮችን ለሀገራዊ ግንባታ እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ተባለ፡፡ 

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ያለመ ኮንፈረንስ በአለም ዓቀፍ የዕውቀት ልውውጥ መረብ የተባለ ሳይንሳዊ ተቋም እና በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በሂልተን ሆቴል ተካሂዷል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ በሀገር ግንባታ ላይ የሚጠቅሙ ትምህርታዊ ምርምሮች ተዳስሰውበታል፡፡

የአለምአቀፉ የዕውቀት ልውውጥ መረብ 1 ሺህ 500 ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አባላት ያሉት ሲሆን፣ አባላቱም በኢትዮጵያ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመዘዋወር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል እያገዙ ይገኛሉ፡፡

የተቋሙ ኃላፊ ፕሮፌሰር አማሬ ደስታ አባላቱ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እያገዙ የሚገኙት ያለምንም ክፍያ በበጎ ፈቃድ እንደሆነና በኢትዮጵያ ያሉትን የሁለተኛ ዲግሪና እና ዶክተሬት ዲግሪ ምሩቃንን አለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በስራ ላይ በየጊዜው ያሉትን አዳዲስ ዕውቀቶችን ማካፈልና ተማሪዎችን በቴክኖሎጂ ማገዝ ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፈሰር ሂሩት ወልደማሪያም በበኩላቸው ምርምርና ዕውቀት ለሀገር ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡት ድጋፍ ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በየአመቱ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ መዘጋጀቱ ነው የተገለጸው፡፡