አይዳ ለታዳጊ ሀገራት 80 ቢሊየን ዶላር ለማሰባሰብ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

የአለም አቀፉ የልማት ትብብር (አይዳ) በ2019 ፕሮግራሙ ለታዳጊ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል 80 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማሰባሰብ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የልማት ማህበሩ አስራ ዘጠነኛውን  የአይዳ 2019 ስብሰባ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል፡፡

ስብሰባው በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተወሰነው ሀገሪቱ ተጨባጭ የምጣኔ ሀብት ሪፎርሞችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኗን ተከትሎ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገልጸዋል፡፡

የአለም ባንክ አካል የሆነው አለም አቀፉ የልማት ትብብር አይዳ ከለጋሽ ሀገራት በየሶስት አመቱ በሚያሰባስበው ገንዘብ ለታዳጊ ሀገራት ድጋፎችን ያደርጋል፡፡

ተቋሙ ባለፉት ሶስት አመታት በየአመቱ በአማካይ ከ19 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሹ ለአፍሪካ ሀገራት የተለገሰ ነው፡፡

በስብሰባው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ ከአይዳ እያገኘች ባለው ድጋፍ ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአይዳ 2019 በቀጣይ ሶስት አመታት 80 ቢሊየን ዶላር ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የአለም ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክሪስታሊና ጎረጂኤቫ በዚህ ገንዘብ ለቀጠናዊ ፕሮጀክቶች በተለይም ለአፍካ ቀንድ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ውጤታማ የሪፎርም ስራ ተከትሎ በአይዳ 2019 ከሚሰበሰበው ገንዘብ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራትም ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡