ኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት የጀመሩበትን 55ኛ ዓመት ሊያከብሩ ነው

ኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት የጀመሩበትን 55ኛ ዓመት ሊያከብሩ ነው

ኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት የጀመሩበት እና የኢትዮጵያ ኤምባሲው መሰረት የተጣለበት 55ኛ ዓመት በዓል ከሰኔ 19-20 ቀን 20011 ዓ.ም በናይሮቢ ሊከበር መሆኑ ተገለጸ።

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ የሚከበረው በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በናይሮቢ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ አማካኝነት ሲሆን፤ ዕለቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ተብሏል።

ኢትዮጵያ ከ55 ዓመት በፊት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና የቀድሞ የኬንያ መሪ ጀሞ ኬንያታ አማካኝነት የኤምባሲዋን መሠረት የጣለችው ሰኔ 1956 ዓ.ም ነበር።

ከኢትዮጵያና ኬንያ የተወጣጡ ባለሃብቶች የሚሳተፉበት የቢዝነስ ፎረምም ዕለቱን በማስመልከት እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን፤  በቢዝነስ ፎረሙ የኢትዮጵያ ምርቶች እና የቱሪስት መዳረሻዎች ለእይታ የሚቀርቡ ይቀርባሉ።

እንዲሁም በናይሮቢ ዩኒቨርስቲና በኤምባሲው የፎቶ እና የስዕል ኤግዚቢሽን የሚቀርብ በመሆኑ የኢትዮጵያን ባህል፣ ሃብት እና እሴት ለኬንያውያን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በናይሮቢ ዩኒቨርስቲ ምሁራን በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ጥናቶች የሚቀርቡ ሲሆን፤ ጥናቶቹ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያለፈበትን ሂደት፣ ተስፋና ዕድሎችን ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።