ታክስ በመሰወር እና ህገ-ወጥ ደረሰኞችን ሲጠቀሙ የተገኙ 166 ድርጅቶች ይፋ ተደረጉ

በገቢዎች ሚኒስቴር ክትትል ሲደረግባቸው የቆዩ ታክስን ለመሰወርና ህገ-ወጥ ተመላሽ ለመጠየቅ ህገ ወጥ ደረሰኞችን የሚጠቀሙ ሀሰተኛ ማንነት ያላቸው 166 ድርጅቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡

በዛሬው እለት በገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና በህግ ተገዢነት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ በተሰጠው መግለጫ በነፍስ ወከፍ ከ51 ሚሊየን ብር በላይ ግብይት የነበራቸው ነገር ግን ባዶ፣ ኪሳራና ተመላሽ ከሚጠይቁ ደርጅቶች መካከል 16 ድርጅቶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ተብሏል፡፡

ከ166 ድርጅቶች መካከል 136 ያህሉ ከ6 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ማድርጋቸውን በመረጃ ቋት ውስጥ መገኘቱን ተነግሯል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጉዳዩን አስመልክተዉ በሰጡት መግለጫ፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የንቅናቄና አጠቃላይ የለዉጥ እንቅስቃሴ የመጣዉን አዎንታዊ ዉጤት አጠናክረን በማስቀጠል በህገ ወጥ ድርጊት ላይ ተሳትፈዉ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ላይ የሚወሰደዉ የህግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለዉም እነዚህ ህገወጥ ድርጅቶች በዋናነት ሃሰተኛ ደረሰኝን የሚያቀርቡ በመሆኑ ግብር ከፋዩ ማንነታቸዉን አዉቆ ምንም አይነት ደረሰኝ ከነሱ እንዳይቀበልና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም እንዳያቀርብ አሳስበዋል፡፡

ድርጅቶቹ ያለደረሰኝ ግብይት ማከናወን፣ ከተጠቃሚ የሚሰበሰበውን ታክስ ለራስ ጥቅም ማዋልና ግብይትን በመደበቅ መንግስት ሊያገኝ የሚገባውን ታክስ አሳጥተዋል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውድድር ሜዳውን ለማስተካከል የህግ ተገዢነት ስትራቴጂን አጠናክሮ በመፈጸምና ህጋዊ እውቅና ለታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ለታማኝ ግብር ከፋዮች በመስጠት ከማስተማር፤ ህጋዊ እርምጃ እስከ መውሰድ የሚችልበት አቋም ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡ (ምንጭ፡-የገቢዎች ሚኒስቴር)