ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ  አህመድ የእውቅና ፕሮግራም ተካሄደ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊነት አስመልክቶ “ሰላም መቶ በመቶ ያሸልማል” በሚል የተዘጋጀው የእውቅና መርሃ ግብር በሚሊኒየም አደራሽ ተካሂዷል።

ዶክተር አቢይ አህመድ የአለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው እና ለሰላም ላበረከቱት አስተዋጽኦ መነሻነት ነው ሀገር አቀፍ የእውቅና ፕሮግራሙ የተዘጋጀው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌደሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሸን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የመግስት ስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኖቤል ሽልማቱ እንደ ሀገር እንድንኮራ ብሎም ለበለጠ እውቅና እንድንዘጋጅ የሚጋብዘን ነው ብለዋል።

ለሰላማዊ መፍትሄ ሁልጊዜ ቀዳዳ እንዳለ የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፥ውይይታችን ከግለሰብና ከቡድን ፍላጎት ባለፈ ብቸኛ ሀገራችን ላይ ያተኮረ መሆን አለበት ብለዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው  የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን፣ እናታቸውን እና ባለቤታቸውን አመስግነዋል።

ሁላችንም በውስጣችን ሰላም ሊኖረን ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በውስጥ ሰላም ከሌለ ወደ ውጭ የሚወጣ ሰላም አይኖርም ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው ሽልማቱ ለአፍሪካዊ የግጭት አፈታት ሂደት እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ሽልማቱ የሁሉም ኢትዮጵያው ነው ያሉት ደግሞ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው።

ወ/ሮ ሙፈሪያት ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ እንድትደርስ ኢትዮጵያውያን ሰውነትን አስቀድመን እንዋደድ ፤ ይህን ማድረግ ከቻልን ሀገሪቱ ከልጆቿ አልፋ ከዓለም ሁሉ ለሚመጡ የተትረፈረፈ ሀብት አላት ነው ያሉት።

በዚሁ መርሃግብር ላይ ስለ ዶክተር አቢይ አህመድ ስብዕና ና እሳቤን የሚያሳይ “አቢይ እንደ ሰው “የሚል ዶክመንተሪም ቀርቧል፡፡