የኢትዮዽያ መከላከያ ሠራዊት የሻዕብያን የማሰልጠኛና የማደራጃ ካምፖች ደመሰሰ

አዲስ አበባ፤የካቲት 6 2004 /ዋኢማ/ – የኢትዮዽያ መከላከያ ሠራዊት በዛሬው ዕለት በወሰደው የማጥቃት እርምጃ የሻዕብያን የማሰልጠኛና የማደራጃ ካምፖች መደምሰሱን የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በመከላከያ ሚኒስቴር  የኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ገብረኪዳን ገብረማርያም ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት የማጥቃት እርምጃው የተወሰደው ራሚድ ገለህቤና ጊንቢ  በሚባሉት የማሰልጠኛና የማደራጃ ካምፖች ላይ ነው፡፡

ከኢትዮዽያ ድንበር ወደ ኤርትራ ዘልቀው በ14፣ 17 እና 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በተቋቋሙት ካምፖች ላይ የተሳካ ማጥቃት በማካሄድ በርካታ የሻዕቢያ ወታደሮች መቁሰላቸውንና መማረካቸውን የገለፁት ኮሎኔል ገብረኪዳን ሻዕቢያ ከጥፋቱ ካልተቆጠበ በቀጣይም ተመጣጣኝና ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

አሸባሪው የሻዕቢያ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ የማተራመስ ስትራቴጂውን ለማሳካት በአካባቢው ያሉ ጸረ ሠላም ኃይሎችን በማደራጀት የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በቅርቡ የአሸባሪው የሻዕቢያ ቅጥረኞች በኢትዮዽያ በአፋር ክልል በጉብሽት ላይ በነበሩ ቱሪስቶች ላይ ጥቃት ሰንዝረው አምስት ገድለው ሁለት ጀርመናዊያንና ሁለት ኢትዮዽያዊያንን ጠልፈው መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡

ይሁንና በኢትዮዽያ መንግሥት በኩል የአፋር የአገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ጥረት ሁለቱ ጀርመናዊያን ሲለቀቁ ሁለቱ ኢትዮዽያዊያን ግን አሁንም አልተለቀቁም፡፡