በምርጫ ዙሪያ ግንዛቤውን ለማዳበር የሚያስችል ትምህርት እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2004 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባለፉት አምስት ወራት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረሰቡ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ላይ ግንዛቤውን እንዲያዳብር የሚያስችል ትምህርት መስጠቱን አስታወቀ፡፡ በትምህርት ስርጭት ላይ ለተሰማሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተዘጋጀ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት በአዳማ ከተማ ተካሄዷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ኘሮሰር መርጊያ በቃና በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለፁት ቦርዱ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ለህብረተሰቡ የመራጮችና ስነ ዜጋ ትምህርት በ11 ቋንቋዎች በመስጠት ላይ ነው፡፡

ቦርዱ ትምህርቱን በመስጠት ላይ ያለው የየክልሎችን ብዙሃን መገናኛ ድርጅቶችን፣ ድምፀ ወያኔን፣ ኢትዮጰያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅትንና ፋና ብሮድ ካስት ኮርፖሬትን በመጠቀም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአገሪቱ የሚካሄዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ህዝቡ በተገቢው ሁኔታ አውቆና ህገ መንግስታዊ መብትና ግዴታውን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ህብረተሰቡ ስነ ዜጋዊ እውቀቱንና ክህሎቱን እንዲያዳብርና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ድርሻውን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የሚዲያ ተቋማት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም እየተገነባ ላለው ዴሞክራሲ ስርዓት የህብረተሰቡ ተሣትፎ እንዲጐለብት ተቋማቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የዓውደ ጥናቱ ዓላማም ባለፉት አምስት ወራት በመራጮችና የስነ ዜጋ ትምህርት ስርጭት ላይ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጐኖችን በመለየት በቀጣይ የተሻለ የስርጭት አድማስ የሚኖርበት ስልት ለመቀየስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት የአገር ውስጥ ቋንቋዎች አስተባባሪና የትምህርት ስርጭት ተወካይ አቶ ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠት እንዲችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የመራጮችና ስነ ዜጋ ትምህርት የምርጫ ስነ ስርዓቱን ለማስከበርም ሆነ ለማክበር ከፍተኛ ቦታ ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ለማስተማሪያነት ያቀረበው ሰነድ በቀጣይነት አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት ዋነኛ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት ለባለሙያዎች በማንዋሉ ላይ በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ ላለፉት አምስት ወራት በተሳካ ሁኔታ ትምህርቱን ሲያሰራጭ መቆየቱንም አስታውቀዋል፡፡

በፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ረዳት ዋና አዘጋጅና በኮርፖሬቱ የትምህርት ስርጭት አስተባባሪ አቶ አዳም ታደሰ እንደገለፁት በመራጮችና ስነ ዜጋ ትምህርት አሰጣጥ ላይ የግንዛቤ ክፍተት እንዳይኖርና ህብረተሰቡ በቀላሉ መረዳት እንዲችል የጋዜጠኝነት ክህሎትና ጥበብ ባካተተ መልኩ ትምህርቱን በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በአፋርኛና በሱማሊኛ ሲያሰራጭ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በአዳማ ከተማ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በተካሄደው የመራጮችና የስነ ዜጋ ትምህርት አሰጣጥ ላይ የተሰማሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አውደ ጥናት ላይ የዘጠኙ ክልሎችና የሁለት ከተማ አስተዳደር ባለሙያዎች ፋና ብሮድካስትና ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ተሣታፊ ሆነዋል፡፡