በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ቦንድ ገዙ

አዲስ አበባ፤የካቲት 7 2004 /ዋኢማ/ – በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬት የ7 ነጥብ 18 ሚሊየን ብር ቦንድ መግዛታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለዋልታ  በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ቦንዱን የገዙት በእንግሊዝ የሚኖሩ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ናቸው።

የሶማሌ ክልል ተወላጆች  በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በክቡር አቶ አብዲ ሞሀመድ ኡመር የተመራ የልዑካን ቡድን በእንግሊዝ ከክልሉ ተወላጆች ጋር ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው ነዋሪዎቹ ለህዳሴው ግድብ ስኬት የቦንድ ግዢውን ያካሄዱት።

ርዕሰ መስተዳድሩ  በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ  በማብራራት በኢንቨስትመንትና በንግዱ ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። 

በእንግሊዝ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ከበደ በበኩላቸው፤ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት መፋጠን ከፍተኛ ሚና እንዳለው መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው መግለጫ አስታውቋል።