የሽብር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ እየተካሄደ ነው -አምባሳደር ዲና

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/ 2006 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት እንዳይከሰት ለመከላከል የሚያስችል ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ከአልሻባብ የሽብር እንቅስቃሴ የጸዳ ባለመሆኑ ኢትዮጵያም ከስጋቱ ነጻ አይደለችም፡፡
በመሆኑም የአልሻባብ የአሸባሪዎች ጥቃት በኢትዮጵያ እንዳይከሰት ለመከላከል የሚያስችል የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ ከጎረቤት አገሮች ጋር በመተባበር በድንበር አካባቢ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሽብር ጥቃትን የመከላከል የዳበረ ልምድ አላት ያሉት አምባሳደር ዲና ስጋቱን ሙሉ በሙሉ ለማሶገድ ህብረተሰቡን ያሳተፍ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ሳመንት በኢትዮጵያ የተካሄደውን አስቸኳይ የመሪዎች ስብሰባ አስመልክቶ እንደተናገሩት ስብሰባው አፍሪካ ወንጀልን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሥልጣን ላይ ባሉ የአፍሪካ መሪዎች ላይ እያካሄደ ያለውን የክስ ሂደት እንዲሰርዝና ሌሎች ጥያቀዎችን የያዘ የአቋም መግለጫ በማውጣት በስኬት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ ፍርድ ቤቱ በስልጣን ላይ ባሉ የኬኒያ መሪዎች ላይ አሁን እያካሄደ ያለው ክስ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የእርቅ ሂደት እያደናቀፈው መሆኑን መሪዎቹ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ 
አምባሳደር  ዲና አያይዘው እንደገለጹት ከአፍሪካ መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ማግስት በተካሄደው  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ ላይ የኢጋድና የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባል ሀገራት በውህደት እንዲሰሩ ሀሳብ እንደቀረበ ተናግረዋል።
በኢትዮዽያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሰብሳቢነት በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ላይ ፥ ውህደቱ በተለይም በአካባቢው የሚነሱ የጸጥታ ጉዳዮችን ፣ የአሸባሪነትና ሌሎች የሰላም ጠንቆችን በጋራ ለመታገል እንደሚረዳ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ለውህደቱ የኢጋድና የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የኢታማዙር ሾሞችና የጸጥታ ሃላፊዎች ከወዲሁ ተቀራርበው ምክክር እንዲያደርጉም ውሳኔ ላይ መደረሱን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡