በሶማሌ ክልል የተደረገው ጉብኝት የተሳካ ነበር: ም/ጠ ሚኒስትር ደመቀ

ጅጅጋ ፤ ጥቅምት 11/2006 /ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲካሄድ የሰነበተው የግል ባለሃብቱና ከፍተኛ የመንግስት ባለስለጠናት ጉብኝት የተሳካና ትምህርት የተወሰደበት እንደነበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ም/ጠ ሚኒስትር ደመቀ የሚመራ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የ9ኙም ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የግል ባለሃብቶችና የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ያሳተፍ ቡድን ክልሉን በመዘዋወር ላለፉት አራት ቀናት ጎብኝቷል።
የልኡካን ቡድኑ በጉብኝቱ በሸበሌ፣ ጀረር፣ ፋፈንና ሲቲ ዞኖች በመንግሰትና በህዝብ የተከናወኑ የልማት ውጤቶችንና የክልሉን የተፈጥሮ ሃብቶችና የኢንቨሰትመንት አማራጮች በተለየ ሁኔታ ትኩረት አድርገው የጎበኙ ሲሆን፤ ክልሉ ለ8ኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል እያደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅትም ጎብኝተዋል።
ቡድኑ ከሲቲ ዞን ጉብኝቱ በኋላ በድሬድዋ ከተማ ባደረገው የማጠቃለያ ውይይት ላይ ም/ጠ ሚኒስትር ደመቀ እንደተናገሩት፤ ቡድኑ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲካሄድ የሰነበተው ጉብኝት የተሳካ እንደነበርና  ለቀጣይም ትምህርት የተገኘበት ነው።
በክልሉ ከብዙ ትግልና መስዋዕትነት በኋላ በተገኘው ሠላምና መረጋጋት መንግስትና ህዝብ መሉ በሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ልማት በማዞር እያከናወኑት ያለው ልማታዊ እንቀስቃሴ ውጤቱ እጅግ እስደሳች መሆኑን ገልጸው፤ በፌደራል መንግስትና በክልሉ መንግስት የተሰሩት ጅምር የልማት ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።
በተለይም አሁን በፈጣን መነቃቃት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉት የልማት ለውጦች አገሪቱ የተያያዘችውን የህዳሴ ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ተናግረው፤ በክልሉ ለተገኘው የሠላምና የልማት ውጤት የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች እንዲሁም የክልሉ ወጣት የአመራር አካላት በነበራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ክልሉ አሁን ፈጣን የልማት ውጤት እያመጣ ቢሆንም አሁንም ገና ብዙ መስራት የሚጠይቅ በመሆኑ መንግስት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀው፤ የክልሉ አመራር አካላትም በተገኘው ውጤት ሳይዘናጉ  ለውጡን  የበለጠ አጠናክረው ለማስቀጠል መረባረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
እንዲሁም በክልሉ በሚገኘውን ሰፊና እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባለሃብቶች እንዲሳተፉ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ በመሆኑ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበው፤ የክልሉ ህዝብም ቡድኑ በየደረሰበት አካባቢ ላደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል።
በውይይቱ ላይ በጉብኝቱ የተሳተፉት ባለሃብቶች በሰጡት አስተያየት ፤ ጉብኝቱ ከዚህ በፊት የነበራቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲለውጡ አስችሏቸዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲባል ቀድሞ የሚመጣላቸው የሠላምና የጸጥታ ችግር ብቻ እንደነበርና የተሳሰተ ግንዛቤ ይዘው እንደነበር ያስታወሱት ባለሃብቶቹ፤ በጉብኙቱ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ጨዋና ሰው አክባሪ ህዝብ፣ ሰፊና ገና ያልተነካ የተፈጥሮ ሃብት በክልሉ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።
ባለሃብቶቹ አዋጭ በሚሏቸው የኢንቨስትመንት መስኮችም ለመሰማራት ፈቃደኞች መሆናቸውንና ሌሎች ባለሃብቶችም ቢሰማሩ ስኬተማ እንደሚሆኑ አስረድተው፤ በጉብኝቱ ወቅት በየደረሱበት አካባቢ ህብረተሰቡ ላደረገላቸው ከፍተኛ የእንግዳ አቀባበል ስነ-ስርዓት አመስግነዋል ።
የፌደሬሸን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በበኩላቸው ፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 8ኛን የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ለማክበር ሃላፊነቱን ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ አመቱን ሙሉ በዓሉን ለማክበር እያደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።