ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አገልግሎቱን በማስፋፋት ላይ መሆኑን ገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2006 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ለተገልጋዮቹ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍፁም አረጋ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ኤጀንሲው በህግ ለደንበኞቹ እንዲሰጥ ከሚጠበቅበት የአገልግሎቶች አይቶች 27ቱን መስጠት ጀምሯል፡፡ ኤጀንሲው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የንግድ ስያሜ ምዝገባ፣ ለደረጃ አንድ ተቋራጮች የግንባታ ፍቃድ መስጠት እንዲሁም ለውጭ ሰራተኞች የስራ ፈቃድ መስጠት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ኤጀንሲው በህግ መስጠት ከሚጠበቅበት አገልግሎቶች ሁለት ብቻ የቀሩት መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ እንዚህንም ቀሪ አገልግሎቶች መስጠት ለመጀመር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት መጀመሩን ነው አቶ ፍፁም የተናገሩት፡፡
በዚህም መሰረት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር መስጠትና የግንባታ ፍቃድ መስጠት ቅድመ ዝግጅቶቹ እንደተጠናቀቁ በኤጀንሲው የሚሰጡ ተጨማሪ አገልግሎቶች እንደሚሆኑ አቶ ፍፁም ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኤጀንሲው ለተግለጋዮች የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተያያዥ አገልግሎቶች እንዲሰጡ በዋና መስሪያ ቤቱ የቢሮ ቦታዎችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑንም ነው አቶ ፍፁም የተናገሩት፡፡
ወደ ሰባት የሚሆኑ የቢሮ ቦታዎች እንደተዘጋጁ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ አንዳንድ መስሪያ ቤቶችም አገልግሎት መስጠት እየጀመሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት በኤጀንሲው በተዘጋጁ የቢሮ ቦታዎች ውስጥ አገልግሎት መስጠት ከሚጀምሩ ተቋማት መካከል ይገኙበታል፡፡