ኢትዮጵያ በኃይል ማምረት የሚሳተፉ ባለኃብቶችን ለመቀበል ዝግጁ ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም

አዲስ አበባ ፤ ጥር 14/2006 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ በኃይል ማምረት ዘርፍ የሚሰማሩ የግል ባለኃብቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም  በአቡ ዳቢ በተከፈተው መፃኢ የዓለም የኃይል አቅርቦት  ዙሪያ በሚመክረው ጉባዔ  ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ሀገራት በኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ነው።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ  ልማት  ስትራቴጂ  ቀርፃ  እየሰራች መሆኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስትራቴጂው የውኃ፣ የንፋስ፣ የፀኃይና  የእንፋሎት ኃይልን ያካተተ ነው ብለዋል።
የፀኃይ ኃይልን ጨምሮ ቀደም ሲል  ውድ የነበሩ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ  ዘርፎች ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን በዓውደ ርዕዩ የተመለከተ ሲሆን ይህም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራትን እንደሚጠቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም መግለፃቸውን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዘገባ አመልክቷል።