ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከሚኖሩ አትዮጵያዊያን ጋር መከሩ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/ 2006 (ዋኢማ) – በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩባቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተለይም ከሀገሪቱ ሰባት ግዛቶች በዱባይ፣አቡዳቢና በአልናያሃ ቁጥራቸው በዛ ያለ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ በሚኖሩባቸው ከተሞችም ማህበር መስርተው በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ  የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በአቡ ዳቢ በነበራቸው ቆይታ ከማህበሩ ኮሚቴ ሀላፊዎች  ጋር ተወያይተዋል፡፡በውይይቱም  ኢትዮጵያዊያኑ  በሀገራቸው ልማት የሚኖራቸውን ተሳትፎ መሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ከውይይቱ በኃላ አስተያየታቸውን ለኢሬቴድ የሰጡ የኮሚኒቲ ኃላፊዎች ፓስተር ዮናስ ፀጋዬና አቶ ይስሀቅ ሀይሌ  ስለ ሀገራቸው የተሰጣቸው ገለፃ የበለጠ በልማቱ እንዲሳተፉ ያበረታታቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 
ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በተባበሩት አረብ ኤምሬት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች አረብ ሀገራት ከሚኖሩት በተሻለ መልኩ ተገቢውን ክብር አግኝተው ይበልጥ እየኖሩ ቢሆንም ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር ጥረቶች እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡በተለይም የሰለጠ የሰው ሀይልን በመላክ ችግሩን ለመከላከል እንደሚሰራ ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡
ወደ ውጭ ሀገራ ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች ተገቢውን ስልጠና ወስደው በመጠኑም ቢሆን ስለሚሄዱበት ሀገር ባህል ግንዛቤ ያላቸው እንዲሆኑ መንግስት የያዘውን አቅጣጫ በተመለከተ ለማህበሩ ኮሚቴ ሀላፊዎች ገለፃ እንዳደረጉላቸው አባላቱ ተናግረዋል፡፡(ERTA)