አካዳሚው የአገሪቱን ህዳሴ ዳር ለማድረስ የሚችል የአመራር ኃይል እያፈራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4/ 2007 (ዋኢማ) – የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የአገሪቱን ህዳሴ ዳር ለማድረስ የሚችል የአመራር ኃይል እያፈራ መሆኑን የማእከሉ ፕሬዝደንት አቶ አዲሱ ለገሰ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ አካዳሚው አሁን ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

አቶ አዲሱ እንዳሉት “አካዳሚው የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ያወቁና በሳይንሳዊ የአመራር ጥበብ የተካኑ ወጣት መሪዎችን የማፍራት ዓላማ  ይዞ በደንብ ተቋቁሞ ስራውን ጀምሯል”።
በተለይም በመለስ ዜናዊ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች የታነጸና በአገሪቱ ያለውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝኃነት ተቀብሎ ዴሞክራሲያዊ አንድነቱን የማስቀጠል አቅም ያለው አመራር ለማፍራት ሚናው የጎላ ይሆናል ብለዋል፡፡
ስልጠናውን የሚሰጠው ከመላው የአገሪቱ ለመጡ ሰልጣኞች በመሆኑ ለባህል ልምድ ልውውጥ ጠቀሜታ አለው ።

በአሁኑ ወቅት አጫጭር ስልጠናዎች ለከፍተኛ፣ መካከለኛና ጀማሪ የመንግስት ኃላፊዎች እየሰጠ ይገኛል።
ከአራት ዓመት በኋላም  የራሱን ካሪክለም በመቅረጽ በአገሪቱ ለየት ያለው አመራርን የማፍራት ዓላማ ያተኮረ ትምህርት ይጀምራልም ብለዋል።
በቀጣይ አድማሱን በማስፋት የሚሰጠው ትምህርት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እንደሚያሳድግም አክለው ገልጿል።

የአካዳሚው ስራዎች በመንግስት በጀት የሚከናወኑ ሲሆን ተጨማሪ ገቢ በስፖንሰር ለማግኘትም ታቅዷል።
አካዳሚው የመንግስት ሓላፊዎችን በማሰልጠን ስራውን መጀመሩ የገለጹት አቶ አዲሱ በቀጣይ በተቋሙ መማር የሚፈልጉ ሁሉ በክፍያ ተጠቃሚ የሚሆኑበትም ስርዓት ይፈጠራል ብለዋል ።
ትምህርቱን ዘመናዊና በአይቲ የታገዘ ለማድረግ በሱሉልታ በ50 ሄክታር ላይ 2 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን የሚያስችል ዘመናዊ ህንፃ እያስገነባ መሆኑንም አቶ አዲስ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 3ሺህ 800 ጀማሪ አመራሮችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል። ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከ30 ሺህ በላይ መካከለኛ አመራሮች፣ 12 ሺህ 800 ጀማሪ አመራሮችና ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛ አመራሮችን አሰልጥኗል።
አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያና በደቡብ ክልል ቅርምጫፎች አሉት። (ኢዜአ)