ቢሮው በአርብቶ አደር አካባቢዎች መስኖን ማዕከል ያደረገ የግብርና ልማት በማካሄድ ላይ ነው

ሀዋሳ፤ ህዳር 5/ 2004/ዋኢማ/–  በደቡብ ክልል በሚገኙ የአርብቶ አደር  አካባቢዎች መስኖን ማዕከል ያደረገ የግብርና ልማት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ::

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው፤ በክልሉ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ከተለመደው የእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን መስኖን መሠረት ያደረገ የእርሻ ሥራዎችን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል::

እርሻን በመስኖ የማልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ የሚገኙት በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ወይጦና የሰገን ወንዞች በሚያልፉባቸው የሐመር፣ የኤርቦሬ፣ የሰላማጎ፣ የዳሰነች እና የኛጋቶም አካባቢዎች ላይ መሆኑን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነትና የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌቱ ዓለሙ ገልፀዋል::

በአሁኑ ወቅት ቢሮው 305 አነስተኛና 10 ትላልቅ የመስኖ ውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮች ገዝቶ ለወረዳዎቹ በማቅረብ በሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉን የሥራ ሂደቱ አስተባባሪ አስረድተዋል ::

ጄኔሬተሮቹ በክረምትም ሆነ በበጋ ወራቶች 1ሺ 29 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳላቸውና በዚህም ከ2ሺ በላይ አባወራ አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል ::

በአሁኑ ወቅት አርብቶ አደሮቹን የእርሻ ሥራ ለማስተዋወቅ ሲባል ለጄኔሬተሮቹ የሚያስፈልጉ የቅባትና የናፍታ ወጪዎች ሙሉ በሙሉ በቢሮው እንደሚሸፈን ነው የገለፁት።

ቢሮው 838 ኩንታል የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ሠሊጥና የተለያዩ የጓሮ አትክልት ዘሮችን ለተጠቃሚ አርብቶ አደሮች ማከፋፈሉን ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪው አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በክልሉ በሚገኙ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ውሃን ማዕከል ያደረገ ልማት በማካሄድ በአንድ ቦታ ተረጋግተው እንዲኖሩ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስተባባሪው መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል::