በሩብ የበጀት ዓመቱ 753 ሚሊየን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ህዳር 5/2004/ዋኢማ/-በተጠናቀቀው ሩብ የበጀት ዓመት ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላኩ ምርቶች 753 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፀው፤ በሩብ የበጀት ዓመቱ 901 ሚሊየን ዶላር ገቢ ይገኛል ተብሎ ታቅዶ የእቅዱን 83 ነጥብ 6 በመቶ ማለትም 753 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

የተገኘው 753 ሚሊየን ዶላር ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ189 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው የተገለፀ ሲሆን፤ በምርት መጠን ረገድም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ እንዳለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ለገቢው መጨመር ምክንያት የሆኑት ወርቅ፣ የቁም እንስሳት፣ የቅባት እህል፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቡና፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ስጋ፣ አበባ፣ ጫት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ ጥራጥሬና የማዕድናት ውጤቶች ወርቅና ታንታለምን ሳይጨምር እንደቅደም ተከተላቸው ሲሆን፤ ሌሎች ምርቶችም እንዳሉ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ ያሳዩ ምርቶች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን፤ የቅባት እቅል፣ የእንስሳት መድሃኒት፣ የተፈጥሮ ሙጫ፣ እጣንና ባህርዛፍ ቅናሽ አሳይተዋል።

ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች መዳረሻ ሀገራት ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የመዳረሻ ሀገሮች ቁጥርን ይበልጥ ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
ዋኢማ