ተጠርጣሪው የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ ህዳር 5/2004/ዋኢማ/–  የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የቀድሞ የትዳር አጋሩ ላይ ከባድ የመግደል ሙከራ ወንጀል ፈጽሟል የጦር መሣሪያም ሳይፈቀድለት ይዞ ተገኝቷል በሚል ክስ የመሠረተበት ተጠርጣሪ ፍስሃ ታደሰ የክስ ሂደት ትናንትም ቀጥሏል።

ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪው ላይ ከባድ የሰው የመግደል ሙከራ ወንጀል እና የጦር መሣሪያ ሳይፈቀድለት ይዞ በመገኘት ወንጀል በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ጉዳዩን እየተመለከተው የሚገኘው የፍርድ ቤቱ ሦስተኛ የወንጀል ጉዳዮች ችሎት ከዚህ ቀደም ባስቻለባቸው ጊዜያት የተከሳሹን የእምነት ክህደት ቃል ተቀብሎ ተከሳሹም ወንጀሉን «አልፈፀምኩም» ብሎ በመካዱ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ ሲመለከት ቆይቷል።

በዚህም ባለፈው ችሎት ፍርድ ቤቱ አራት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን አድምጧል። በትናንቱ ውሎው ደግሞ የተጎጂዋንና የዓቃቤ ሕግ ምስክር የሆነችውን አበራሽ ኃይላይን የምስክርነት ቃል ሰምቷል።

ለወትሮው ጉዳዮችን ሲያይ ከነበረበት መደበኛው አዳራሽ የበለጠ ወደሚሰፋው አንደኛ ወንጀል ችሎት አዳራሽ የተዘዋወረው ሦስተኛ የወንጀል ጉዳዮች ችሎት በርካታ ታዳሚ በተገኘበትና በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ የተጎጂዋን የምስክርነት ቃል አድምጧል።

የችሎቱ ዳኞች ተሰይመው የክሱን መዝገብ ማየት በጀመሩ ጊዜም ተጎጂዋ ቀርባ የምስክርነት ቃሏን እንድትሰጥ ተጠራች።

በአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቸር) ላይ ተቀምጣ ጥቁር ልብስና ጥቁር መነፅር አድርጋ በዳኞቹ መግቢያ በር ወደ ችሎቱ ስትገባም በአዳራሹ ያለው የችሎቱ ታዳሚ ከንፈር በመምጠጥና በልቅሶም ጭምር ተቀብሏታል።

ተጠርጣሪው አቶ ፍስሐም ድምፁን ከፍ አድርጐ «ስለፈጠረሽ ብለሽ እውነቱን ተናገሪ» እያለ ሲያለቅስ ታይቷል። ችሎቱም ለተከላካይ ሁለት ጠበቆች ደንበኛቸው ከችሎት ሥርዓት ውጪ እየሆነ መሆኑን ገልፆ፤ ሥርዓት እንዲያስይዙት ጠይቋል።

ተከሳሹም ዝም በማለት ቀሪ የችሎቱን ሂደት ተከታትሏል። የግል ተበዳዩዋን በምስክርነት ያቀረበው ዓቃቤ ሕግም ዋና ጥያቄዎቹን ለተጎጂዋ አቅርቧል። ተጎጂዋም በአቶ ፍስሐ ላይ ሰፊ የምስክርነት ቃል ሰጥታለች።

ተጎጂዋ በሰጠችው ምስክርነት ከተከሳሹ ጋር የነበራት ጋብቻ ከፈረሰ በኋላ «በሠለጠነና በጓደኝነት ግንኙነታችን መቀጠል እንችላለን» ብለው መስማማታቸውን፤ በዚሁም መሠረት ይገናኙ እንደነበር አስረድታለች።

ይሁንና ብዙ ጊዜ ተከሳሹ ስልክ እየደወለ እንዲገናኙ በሚጠይቃት እና እሷ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች እንደማይመቻት ስትገልፅለት ዛቻና ማስፈራራት ያደርስባት እንደነበርም ተናግራለች።

ዛቻና ማስፈራራቱን በመፍራትም እሱም እየደወለ፤ እሷም እየደወለች ይገናኙ እንደነበርም አክላለች።

ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የደረሰባትን ባስረዳች ጊዜም መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ገደማ ወደ ቤቷ ስታቀና ተከሳሹ እንደ ደወለላትና ሊያገኛት እንደሚፈልግ ገልጾላት ከምሽቱ 4፡30 ገደማ ቤቷ ድረስ መምጣቱን ተናግራለች።

ቤት ውስጥ እያሉም ቴሌቭዥን ላይ የተቀመጠ የእሷን ፎቶ ከተመለከተ በኋላ የእሱን ፎቶ ለምን ከእሷ ጋር አብራ እንዳላደረገችው ጠይቋት፤ እሷም ፎቶውን እዛ እንደማታደርግ በመንገር በቀጣዩ ቀን ሥራ ስላላት ወደ ቤቱ እንዲሄድ እንደጠየቀችው ገልጻለች።

ከዚያም ስጦታ አምጥቼልሻለሁ ብሎ ከኪሱ ሽጉጥ አውጥቶ ወደ ግድግዳው ካነጣጠረ በኋላ ቁጭ እንድትል እንዳስገደዳት፣ በሽጉጡም ፊቷንና ጭንቅላቷን እንደመታት፣ በእጁና በእግሩም ደጋግሞ እየረጋገጣት ጉዳት እንዳደረሰባት ተናግራለች።

ወዲያውም ሮጣ ወደ መኝታ ቤት ስትሄድ ፀጉሯን እየጎተተ ወደ ሣሎን መልሶ እንደደበደባት፤ ከዚያ ከኪሱ ስለት አውጥቶ የግራ ዓይኗን ሙሉ በሙሉ እንዳፈሰሰው፤ የቀኝ ዓይኗንም እንዳጠፋው፤ ስትከላከልም ጣቶቿ በስለት መጎዳታቸውን አስረድታለች።

ዓይኗ ውስጥም በጣቱ ሊገባ ሲታገላት እንደምታስታውስ፤ ከዚያ በኋላ ራሷን መሳቷን፤ ኋላ ላይ አንድ ሰው መጥቶ ፖሊስ መሆኑን እንደነገራትም ገልጻለች።

በታይላንድ ባንኮክ በተደረገላት ሕክምና ጭንቅላቷ ውስጥ ደም መፍሰሱን፤ ግራ ዓይኗ ሙሉ በሙሉ መፍሰሱ፤ ቀኝ ዓይኗ ደግሞ ነርቩ ተነክቶ ከጥቅም ውጪ መሆኑን፤ የግራ ፊቷ ክፍል መደንዘዙን፤ ወገቧ ለመቆም እንደማያስችላትና በጣቶቿ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባትም ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።

ተጎጂዋን መስቀለኛ ጥያቄ እንዲጠይቁ የተደረጉት የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቆች በደረሰባት ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው፤ በሰጠችው የምስክርነት ቃል ላይ ጥያቄ አቅርበውላታል።

ጠበቆቹ ወንጀሉ ተፈፀመ በተባለበት ምሽት አቶ ፍስሐ ቤቷ እንዲመጣ ፈቅዳለት መሆን ያለመሆኑን ጠይቀው፤ እንዳትመጣ ያለማለቷን እና ከዚያ በፊትም ቤቷ ይመጣ እንደነበር መልሳለች።

ወንጀሉ ከመፈፀሙ በፊትም ስለሚዝትና ስለሚያስፈራራት እንደሚገናኙ የሰጠችውን ምስክርነት መሠረት በማድረግም በፈቃዷ ትጋብዘው አትጋብዘው እንደነበር እንድትመልስ በጠበቆች ስትጠየቅም እንደምትጋብዘው አመልክታ፤ ይህንን የምታደርገው ግን እሱ በደወለ ጊዜ እሱ ብቻ እንደሚደውልና ለምን እሷስ እንደማትደውልለት አጥብቆ ስለሚናገራት መሆኑንም አስረድታለች።

ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ከፍስሐ ጋር የተነጋገሩት ነገር መኖር አለመኖሩን ስትጠየቅም «አላስታውስም» ብላለች። «በረደኝ አልብሰኝ» አላልሽውም ወይ? ተብላ በጠበቆች ስትጠየቅም ዓቃቤ ሕግ የመስቀለኛ ጥያቄን ሕጋዊ አግባብ በማንሳት ተቃውሟል።

ወዲያውም ጠበቆች ተቃውሞውን ተቀብለው ጥያቄያቸውን ቋጭተዋል። ዓቃቤ ሕግም በድጋሚ ጥያቄው ተጎጂዋ ከአቶ ፍስሐ ጋር ትገናኝ የነበረው ስለሚዝትባት መሆኑን አስረግጣ እንድታስረዳ የሚያደርግ ጥያቄ ጠይቆ ተጎጂዋም ይህንኑ አድርጋለች።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በማጣሪያ ጥያቄው ጊዜ አለመግባባት መኖሩን ጠይቆ ተጎጂዋ እሱ ደውሎ እንደአጋጣሚ የማይመቻትና የማይገናኙ ከሆነ አለመግባባት ይፈጠር እንደነበር አውስታለች። ከፍቺያቸው በኋላ ለምን ግንኙነታቸው እንደቀጠለ ፍርድ ቤቱ ጠይቆም «በሠለጠነ መልኩ እንደ ጓደኛ እንድገናኝ ተስማምተን ነው» የሚል ምላሽ ከተጎጂዋ ተሰጥቷል።

በፍፃሜውም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ከባድ የሰው መግደል ሙከራ እና ሳይፈቀድለት የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል መከሰሱን አውስቶ፤ ተጎጂዋን ጨምሮ አምስት ምስክሮች የጽሑፍ፣ የኤግዚቢትና የፎቶ ግራፍ ማስረጃዎች በዓቃቤ ሕግ መቅረባቸውን ገልጿል።

ማስረጃዎቹን ከመረመረ በኋላም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 142 መሠረት በሁለቱም ወንጀሎች የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

የተከሳሽን የመከላከያ ማስረጃ ለማየትም ለኅዳር 12 ቀጠሮ የተያዘ ሲሆን፤ ተከላካይ ጠበቆች ተጎጂዋ አንዷ የመከላከያ ምስክር መሆኗን ጠቅሰው፤ ለሕክምና ወደ ውጭ የምትሄድ ከሆነ ለነገ ትሰማልን በሚል አመልክተዋል። ፍርድ ቤቱም እሷን በምስክርነት መጥራት የሚቻል ቢሆንም፤ ለእሷ መጥሪያ ባልተሰጠበት ሁኔታ ምስክርነቷን መስማት የሚያስችል ሥርዓት ያለመኖሩን አብራርቷል።

በሌላ በኩል ዓቃቤ ሕግ «ተከሳሹ ከችሎት ሲወጣ ለችሎቱ ታዳሚ ያልተገባ ባህርይ ያሳያልና ይታረም» በሚል ካመለከተና ጠበቆቹም በጥብቅ እጀባና ቁጥጥር ስር ሆኖ ይህንን ያደርጋል ለማለት አይቻልም፤ ዓቃቤ ሕግም ለዚህ አቤቱታው ማስረጃ የት አለው በማለት ተቃውመዋል።

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ እንዲያቀርብ እንደማይጠበቅበትና የችሎቱን ሥነ ሥርዓት ማስከበር የግራ ቀኙም ኃላፊነት መሆኑን አሳስቧል።

በተያያዘ ዜና ተጎጂዋ የበረራ አስተናጋጅ አበራሽ ኃይሌ ለፍርድ ቤት ቃሏን ከሰጠች በኋላ ከቀኑ በአስር ሰዓት ገደማ በሸራተን አዲስ መልዕክት አስተላልፋለች።

ትናንት ጠዋት ከታይላንድ የመጣችውና ወደዚያው ተመልሳ የምታቀናው አበራሽ « በብሬል ማንበብ ችዬ እያነበብኩ ሃሳቤን ብገልፅ ደስ ባለኝ ነበር። ግን አልችልም» ካለች በኋላ መልዕክቷን በሌላ ሰው አስነብባለች።

በመልዕክቷም በተፈፀመባት ወንጀል አዝነው ከጎኗ ላልተለዩ ሁሉ ምሥጋና አቅርባለች። ለብዙኃን መገናኛዎች አሃዱ ያለችውን ምሥጋናዋን ለኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፤ ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሠራተኞቹ ሙሉ የሕክምና ወጪዋን እየሸፈኑ ላሉት ለሼክ መሐመድ አላሙዲና ከጎኗ ለቆሙ ሁሉ ምሥጋናዋን ሰጥታለች።

«በሴቶች ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየተባባሳ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው እኔም የዚህ ጥቃት ሰለባ በመሆን ብርሃኔን አጥቻለሁ። በሌላው አካሌም ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶብኛል። ሕክምናዬም ገና በተገቢው ሁኔታ አልጨረስኩም። ከሁሉም በላይ ልቤ ተሰብሯል።» ስትል መናገሯን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።