ምክር ቤቱ የግጭት አፈታት ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ

ሀዋሳ፤ መጋቢት 6 2004/ዋኢማ/ – የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ክልላዊ የግጭት አፈታት ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ።

በምክር ቤቱ የብሄረሰቦች የጋራ እሴቶች ማጎልበትና አለመግባባቶችን መፍታት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ዘለቀ በላይነህ ለዋልታ እንደገለፁት የተነደፈው ስትራቴጂ አልፎ አልፎ በክልሉ የተለያዩማህበረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶችን በሠላም ለመፍታት ያስችላል፡፡

የግጭት አፈታት ስትራቴጂው በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች እና ሌሎች ባለድርሻ   አካላት  በግጭት መከላከል እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያላቸውን ሚና፣አወቃቀር፣ አሠራር፣ግንኙነት እና አደረጃጀት ግልጽ እና ወጥ በማድረግ በተቀናጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ እንደሚያስችል የሥራ ሂደት ባለቤቱ  አስረድተዋል፡፡

ክልሉ ቀደምሲል ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን አስቀድሞ ከመከላከልና ከመፍታት ይልቅ ግጭቶች ከተከሰቱ እና በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ባለፈው ዓመት አጋማሽ የተዘጋጀውና በተያዘው ዓመት ተግባራዊ መሆን የጀመረው ስትራቴጂ በክልሉ የግጭት መነሻ የሚሆኑ አስተዳደራዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አስቀድሞ ለመለየትና መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል።ስትራቴጂው የክልሉ ዕድገት በዘላቂ ሰላም ላይ የተመሠረተ እንዲሆንም አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አቶ ዘለቀ  አመልክተዋል፡፡

ስትራቴጂው በክልሉ እስከአሁን የተከሰቱ ግጭቶች መንስኤዎቻቸውን እና ባህሪዎቻቸውን በማጥናት እና በመመርመር መዘጋጀቱን አቶ ዘለቀ ጠቁመው ባህላዊና ሳይንሳዊ የግጭት መከላከል ዘዴዎችን አጣምሮ መያዙንም አስረድተዋል።

ስትራቴጂው በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሠፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በዘርፉ ምሁራን በማስተቸት በማጠናከሪያ ሀሳቦች እንዲዳብር መደረጉን የሥራ ሂደት ባለቤቱ  ተናግረዋል፡፡

ድህነት ፤የመልካም አስተዳደር አጥረት፤ የመቻቻል ባህል ያለመዳበር ፤ የራስ አስተዳደር የመፍጠር እና የድንበር ጥያቄዎች በክልሉ ዋነኛ የግጭት ምክንያቶች መሆናቸውን የዘረዘሩት የሥራ ሂደት ባለቤቱ ስትራቴጂው የችግሮቹን መንስኤዎች ደረጃ በደረጃ በመፍታት ለክልሉ ልማትና ዕድገት መፋጠን ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል ፡፡