የኢትዮጵያን የአበባ ምርት በአሜሪካ ለማስተዋወቅ ባለድርሻዎች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6 2004 /ዋኢማ/ -የኢትዮጵያን የአበባና የፍራፍሬ ምርት በሰሜን አሜሪካ ለማስተዋወቅ የዘርፉ ባለድርሻዎች የተቀናጀ ሥራ መስራት እንዳለባቸው በአሜሪካ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ግርማ ብሩ ገለፁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በዋሽንግተን ለእይታ በቀረበበት ወቅት  የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ግርማ ብሩ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በአበባ ምርት ከአፍሪካ የመሪነቱን ሥፍራ በመያዝ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የአበባ አምራችና ላኪ አገር ለመሆን የበቃችው ከጥቂት አመታት ወዲህ በሀገሪቱ መንግስት ባደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአበባና የፍራፍሬ ምርት በዋነኛነት መዳረሻው የአውሮፓ ሀገራት እንደነበር ያስታወሱት  አምባሳደሩ፤ ምርቱ በተለይም በሰሜን አሜሪካ ሰፊ ገበያ እንዲኖረው ለማስቻል የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች፣ የአሜሪካ ሜትሮፖሊታን ኤርፖርቶች ባለስልጣናት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የሆልቲካልቸር ኤጀንሲና የኢትዮጵያ አበባ አምራችና ላኪዎች ማህበር በጋራ በመሆን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። 

በዋሽንግተን እየተካሄደ ያለው አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ በአበባ ምርት ከፍተኛ አቅም እንዳላት ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረው፤ የኢትዮጵያ ላኪዎችና የአሜሪካ የአበባ ምርት ገዢዎችን ግንኙነት የበለጠ ሊያጠናክረው እንደሚችል ተስፋ አለኝ ብለዋል።

የአሜሪካ ሜትሮፖሊታን ኤርፖርቶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጆን ፖተር በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በሰፊ የአሜሪካ ገበያ ውስጥ እንዲገባ መንግስታቸው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሆልቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ኃይለስላሴ ተክኤ እና  የኢትዮጵያ አበባ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ፀጋዬ አበበ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የሆልቲካልቸር ምርት በመላው አለም ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአበባ ምርት ለእይታ በቀረበበት ወቅት ከሁለቱ ሀገራት የተውጣጡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የኢትዮጵያ አበባ ላኪዎች፣ የአሜሪካ አበባ ምርት ገዢዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ የሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የላከው መግለጫ ያስረዳል።