አፍሪካ ልማት ባንክ የኢትየጵያን እድገት አደነቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2006 (ዋኢማ) – የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት ያሳየችው አስደናቂ እድገት ሀገሪቱ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ለማሳካት በሚያስችላት ደረጃ እንዳደረሳት ገለጸ፡፡

አፍሪካ ልማት ባንክ እና ኢትዮጵያ- ጥምረት ለሁሉን አቀፍ እድገት በሚል በቅርቡ ባወጣው ጽሁፍ ባንኩ ሀገሪቱ የምታካሂደው ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታና የግብርናው ዘርፍ ገበያ ተኮር መሆን ለባለ 11 በመቶው እድገት ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡

ባንኩ የመንግስት ፖሊሲ ለሁሉን አቀፍ እድገት ትልቅ ሚና እንደነበረው አመልክቶ 69 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ በጀት ባለፈው አመት በጀት እንኳ ደሀ ተኮር በሆኑ ስራዎች ላይ ያተኮረ እንደ ነበር አሳይቷል፡፡

የመንግስት ጥንቃቄ የተሞላበት የገንዘብ ፖሊሲ ከሁለት አመታት በፊት እስከ 40 በመቶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ወደ 7.7 በመቶ እንዳወረደው ባንኩ በጽሁፉ አመላክቷል፡፡ ባንኩ የሀገሪቱን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከግምት በማስገባት ትብብሩን እንደሚቀጥል ጠቁሟል፡፡

የሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ እና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ መስራት አስተማማኝ ውጤት እንደሚያስመዘግብ እምነት ያለው ባንኩ ከሀገሪቱ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቋል፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ ባንኩ በቅርቡ የኢትዮ ጂቡቲን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የኬንያ ኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የሞምባሳ ናይሮቢ አዲስ አበባን የመንገድ ስራ እና የገጠር ውሀ አቅርቦትና ንጽህና ፕሮግራም በፋይናንስ እየደገፈ ያለውም ከዚህ እምነቱ በመነሳት ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ባንኩን የዛሬ 50 አመት ከተቀላቀለችበት ግዜ ጀምሮ የ3.75 ቢሊየን ዶላር ብድርና እርዳታ ያገኘች ሲሆን ባንኩ ከፍተኛ ብድር ከሰጣቸው መሀከል 6ኛዋ ሀገርም እንደሆነች ጽሁፉ ይጠቁማል፡፡