የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ሁለት ዘመናዊ ቴሌስኮፖችን በእንጦጦ አካባቢ ሊተክል ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 8 ፤ 2006 (ዋኢማ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ   በሃገሪቱ  የህዋ ምርምር  ትልቅ  አስተዋጽኦ ማድረግ   የሚያስችሉ   ሁለት  ዘመናዊ ቴሌስኮፖችን  ወደ ሃገር  ውስጥ  በማስገባት   በእንጦጦ አካባቢ ተከላቸውን ሊያከናወን  መሆኑን  ገለጸ ።

የእንጦጦ ኦብርዘርቫቶሪ  ዳይሬክተርና  የሕዋ ሳይንስ ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን በላይ እንደገለጹት  ሁለቱ የህዋ ምርምር   ቴሌስኮፖች  ከጀርመን  የቴሌስኮፕ አምራች  ኩባንያ ከሆነው አስቴልኮ   በ 2 ነጥብ 3ሚሊዮን  ዩሮ  ወጪ  ግዢያቸው መፈጸሙን  ተናግረዋል ።
በእንጦጦ  አካባቢ የሚተከሉት  ሁለቱ  ቴሌስኮፖች  እያንዳንዳቸው  የአንድ ሜትር ስፋት እንዳላቸው የተናገሩት  ዶክተር ሰለሞን  ቴሌስኮፖቹ  የሕዋ ሳይንስ  ምርምር በሃገር ውስጥ ለማድረግ ከመርዳታቸውም በላይ በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች  የሚማሩ ተማሪዎችን  ዕውቀት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል ።

ሁለቱ    ቴሌስኮፖች በአሁኑ ወቅት  በለገጣፎ  አካባቢ በሚገኝ  መጋዘን እንደሚገኝ የጠቆሙት  ዶክተር  ሰለሞን  በጥቅምት 9 2006  ዓም   ወደ  እንጦጦ አካባቢ በተዘጋጀላቸው  ቦታዎች   ለመተከል  ዝግጅቱ  መጠናቀቁን  አያይዘው  ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ  ሶሳይቲ  ከስምንት ዓመት በፊት ሲቋቋም  ብዙዎች  የሞኞች  ስብስብ ብለው እስከመሳለቅ  ደርሰው  እንደነበር ያስታወሱት   ዶክተር ሰለሞን   አሁን ሶሳይቲው  በ80 ሚሊዮን ብር  የምርምር ማዕከሉ  ግንባታውን   በማጠናቀቅ    በጥቅምት ወር ሥራ እንደሚጀመርና  የበርካታ ስኬት  ባለቤት እየሆነ እንደሚገኝ አብራርተዋል ።

ከአስር  ዓመት  በፊት  በዘርፉ   አንድ  ዶክተር ባለሙያ  ብቻ እንደነበር   የጠቀሱት ዶክተር ሰለሞን   በአሁኑ ወቅት  በአገሪቱ  በዘርፉ   የሠለጠኑ 8  ዶክተሮችና   45  የማስተርስ  ዲግሪ ያላቸው ዜጎች በመኖራቸው  በምርምር ማዕከሉ በአብዛኛው  ኢትዮጵያውያንና  ጥቂት የውጪ ባለሙያዎች  ሥራውነ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ  ስፔስ ሶሳይቲ   ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካና   የአለም አቀፉ የሕዋ ሳይንስ  ሶሳይት  አባል  እንድትሆን በማስቻሉ  ኩራተ እንዳሚሰማው  የገለጹት  ዶክተር ሰለሞን   ለወደፊቱም  የክልላዊ  የ ሕዋ  ሳይንስ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ   የመሆን እድሉ ሰፊ እንደሆነ  ጠቁመዋል ።

የኢትዮጵያ  ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ   የቦርድ ሊቀመንበር  አቶ ተፈራ ዋልዋ  መንግሥት  ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት  ውስጥ  ለሕዋ ምርምር ፤ ለግንኙነትና   ለደህንነት  የሚያገለግሉ   ሶስት ሳተላይቶችን   ወደ  ሕዋ ለመላክ  እቅድ  እንዳለው   ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ  ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ  በ 1996 ዓም  የተቋቋመ ሲሆን  በአሁኑ ወቅት 49  መሥራች አባላት ፤ 1ሺ 8 መቶ አባላትና   9 ዕህፈት ቤቶችን  በመላ ሃገሪቱ ከፍቷል ።