ሶማሌ ክልል እየተመዘገበ ያለው የሠላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ም/ጠ ሚኒስትር ደመቀ አስታወቁ

ጅጅጋ፤ ጥቅምት 9/2006 /ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተመዘገበ ያለው የሠላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

 

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው የመንግሰት ባለስልጣናት፣ የባለሃብቶችና የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች ቡድን ከባለፈው ሀሙስ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ጉብኝት እያካሄደ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው የመንግሰት ባለስልጣናት፣ የባለሃብቶችና የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች ቡድን በጎዴ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የጎሳ መረዎችና የሀገር ሽማግሌዎች፤ እንዲሁም የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።
ቡድኑ በጎዴ የግብርና ኮሌጅ የመሰብሰቢያ አደራሽ ከክልሉ የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረገው  ውይይት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት ፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተመዘገበ ያለው የሠላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባሮች አበረታች ናቸው።
በክልሉ ከዚህ ቀደም በነበረው ያልተረጋጋ የሠላምና የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በክልሉ ልማትንና መሰረተ የልማት አውታሮችን ለመዘርጋት አስቸጋሪ እንደነበረ ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ጥቂት አመታት እየተገነባ ባለው አመራር፣ በአካባቢው ህብረተሰብ ቀጥተኛ ተሳትፎና በሀገር መከላከያ ሰራዊት የተቀናጀ ስራ አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ልማትን ማድረስ እየተቻለ ነው ብለዋል።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና ንጹህ ውሃን በማዳረስ ረገድ የተሰሩ ስራዎች አበረተች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በክልሉ  የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች ችግሮችን በመፍታት ከህብረተሰቡ ጎን በመሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በክልሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ አስተዳደር መኖሩን በመጠቆም ባለሃብቶች ወደ ክልሉ በመምጣት እንዲያለሙ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይት መድረኩ የአካባቢው ማህበረሰብ በክልሉ የስልክ፤ የመብራት፣ የመንገድ፣  የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደሚስተዋሉና መንግስት ችግሮቹን እንዲፈታላቸው  ላነሱት ጥያቄዎች መንግስት ጥያቄዎቻቸውን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን  ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  አብዲ መሀመድ ኡመር በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ባካሄዳቸው ርብርቦሽ በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ በመሆኑ፣ ያለው አስተዳደር ምቹ በመሆኑና እምቅ ያልተሰራበት የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም ባለሃብቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡና መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በጉብኝቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የፌደራል ተቋማት ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና የክልሉ የአገር ሽማግሌዎች እየተሳተፉ መሆናቸወን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።