አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12 ፤ 2006 (ዋኢማ) – በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እየተከናወነ ባለው የአርብቶ አደር ልማት ፕሮጀክት 2ነጥብ 98 ሚሊዮን የሚሆኑ አባውራና እማውራ አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ ።
በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የአርብቶ አደር ማህብረሰብ ልማት ፕሮጀክት ተጠባባቂ አስተባባሪ አቶ ሰይድ ዑመር ለዋልታ እንደገለጹት በጥር 2001 ዓም የተጀመረው የአርብቶ አደሩን ያሳተፈው የልማት ፕሮጀክት እስካሁን በመጠጥ ውሃ ፤ በእንስሳት እርባታ ፤በትምህርት ፤ በሰውና በጤና ኬላዎች ፤ በመንገድና የመስኖ ልማት ዘርፎች 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚሆኑ የአርብቶ አደሩ አባውራዎችና አማውራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
በአርብቶ አደሩ ልማት ፕሮጀክት በአፋር ፤ ጋምቤላ ፤ቤኒሻንጉል ፤ ሶማሌና አርብቶ አደር ባለባቸው የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰኢድ በታህሳስ ወር 2006 ዓም የሚጠናቀቀው ሁለተኛው የፕሮጀክቱ መርሃግብር 55 ወረዳዎች ያካተተ መሆኑንና እስካሁን 1 ነጥብ 49 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አያይዘው ተናግረዋል ።
በአርብቶ አደሩ የቁጠባ ባህልን እንዲያጎለብት ከፌደራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር 29 ሺ 441 አባላት ያሉት 448 የብድርና ቁጠባ ተቋማት 19ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ቆጥበዋል ያሉት አቶ ሰይድ የአርብቶ አደሩን ያኗኗር ዜይቤ እየተቀረ መምጣቱን የጠቆመ ነው ብለዋል ።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ በመቀመር ሌሎች አርብቶ አደሮች እንዲጠቀሙበት ለማስቻል የልምድ ልውውጥ በየጊዜው እንደሚከናወን የጠቀሱት አቶ ሰይድ አንዱ ከሌላው እንዲማር ማገዙን ገልጸዋል ።
በፌደራል ሚኒስቴር ሥር በሚከናወነው የአርበቶ አደር ማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክት በ ሶስት አምስት ዓመታት ተከፋፍሎ ለ 15 ዓመታት የሚካሄድ ሲሆን ሶስተኛው መርሃ ግብር በጥር 2006 እንደሚጀመርና ከአለም ባንክ ና ከአለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ቃል በተገባ የብድር ገንዘብ ለማከናወን መታቀዱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።