የቀላል ባቡር ግንባታ ተገጣጣሚ ድልድዮችን የመዘርጋት ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12 (ዋኢማ) – የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ግንባታ ተገጣጣሚ ድልድዮችን የመዘርጋት ስራ ተጀመረ፡፡

በመጪዎቹ ሳምንታት ደግሞ ባቡሩ በሚያልፍባቸው መስመሮች የሀዲድ ዝርጋታ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ የምደር ባቡር ኮርፖሬሽን ገለፀ፡፡

በመሬት ላይና በምድር ውስጥ እንዲሁም በድልድዮች ላይ በሚደረገው የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ጉዞ የግንባታ ፕሮጀክት ከተጀመረ ወዲህ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ቀላል ባቡሩ በድልድዮች ላይ በሚያልፉባቸው መስመሮች 299 ቀላል ቋሚ ምሶሶዎች ቆመዋል፡፡

በእነዚህ ምሶሶዎች ላይ ደግሞ በፕሮጀክቱ ሲመረቱ የቆዩ 510 ድልድዮች ይገጣጠማሉ፡፡

በዚህ አመት የፕሮጀክቱ ወሳኝ ተግባራት ከሆኑት ውስጥ ይሀው ድልድዮችን የመገጣጠም ስራ ደግሞ ጎተራ አከባቢ ተጀምሯል፡፡

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር በሃይሉ ስንታዮህ እንዳሉት እስከ መጪው ግንቦት በተለያዩ ቦታዎች ድልድዮችን የመገጣጠም ስራው ይቀጥላል፡፡ በመጪዎቹ ሳምንታት ደግሞ ሀዲድ የማንጠፍ ስራዎች እንደሚጀመሩ ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር በ2007 ዓ.ም ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም የኢትዮጵያ የምደር ባቡር ኮርፖሬሽን ገልጿል፡፡

እስከ 2005 ዓ.ም ከሰው ሃይልና የመሳርያ ንቅናቄ አንስቶ ያለው የፕሮጀክት አጠቃላይ አፈፃፀም 43 በመቶ ያህል መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በያዝነው ዓመት ደግሞ ፕሮጀክቱ ከ80 በመቶ የሚበልጥ ስራው ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር ወደ 34 ኪሎሜትር የሚጠጋ ርዝመት አለው፡፡