የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2006/ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ዛሬ ተጀመረ።

ጉባዔው በቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ በተጀመረበት ወቅት ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት፤ ጉባዔው ለቤተ ክርስቲያኗና ለሀገሪቱ እድገትና ልማት የሚጠቅሙ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ ልዩ ልዩ ውሳኔችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ሃይማኖትን ማስፋፋት፣ መማርና ማስተማር የሚቻለው በህዝቦች መካከል እኩልነት፣ መቻቻል፣ መተማመን፣ መፈቃቀር፣ መስማማት፣ አንድነት፣ ፍፁምና አስተማማኝ የሆነ ሰላም ሲሰፍን ነው ብለዋል።

በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ችግሮችን በውይይትና በጋራ የመፍታት ባህልን በማጎልበት በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለውነ ሰላም፣ እኩልነት፣ መቻቻል፣ መከባበር፣ መተማመን፣ ወንድማማችነትና የልማትና የዕድገት ጅምርን ሊፈታተኑ የሚችሉ የአክራሪነት፣ የአሸባሪነትና የጽንፈኝነት ተግባራትን በማውገዝ የክርስቶስ መልዕክት የሆነውን ሰላምና ፍቅርን፣ አብሮ መልማትና ማደግን ለህዝቡ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ ይገባል ሲሉም አሳስዋል።

በጉባዔው ላይ ከሁሉም ሀገረ ስብከት የተውጣጡ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት ተሳታፊ መሆናቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።