ኢትዮጵያ የቀጠናዋ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል እንድትሆን ተመረጠች

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2006 (ዋኢማ) – የ14 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የስነ-ፈለክ ጥናት ማስተባበሪያ ክፍለ አህጉራዊ ፅህፈት ቤት በአዲስ አበባ ሊከፈት ነው፡፡

በህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በሚሰራው ዓለማቀፉ የስነ-ፈለክ ህብረት /IAU/ ከኢ.ፌ.ድ.ሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ጋር በህዋ ሳይንስ ዙሪያ የዓለማቀፍ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ጥር 2/2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂሚንስትሯ ወ/ሮ ደሚቱ ሀምቢሳ እንዳሉት ስምምነቱ በአፍሪካ ዋንኛ ችግሮች እየሆኑ ለመጡት እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የውሃ ሀብት አጠቃቀም፣ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ክስትቶችን በወሰን ተሻጋሪ የውሀ ሀብት ላይ የሚነሱ ግጭቶችን ለመቆጣጠርና በቀጠናው ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡

እንደ ሚንስትሯ ገለፃ የህዋ ተኮር ጥናቶችና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀምም በውሀ ሀብት አስተዳደርና ዘላቂ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ እክሎች ላይ መፍትሄዎችን ለማስገኘት ያግዛል፡፡

የአለም አቀፉ የስነ-ፈለክ ህብረት /IAU/ ዳይሬክተር ኬቨን ጎቬንደር በበኩላቸው በአዲስ አበባ የሚከፈተው ክፍለ አህጉራዊ ፅህፈት ቤት ከአፍሪካ የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአለም ላይ በቻይናና በታይላንድ የክፍለ አህጉራዊ ፅፈት ቤቶች መኖራቸውንም የገለፁት ኬቨን ፣በቅርቡ የበደቡባዊ አፍሪካን የስነ-ፈለክ ጥናት ማስተባበሪያ ክፍለ አህጉራዊ ፅህፈት ቤት በደቡብ አፍሪካ ኬፕታዎን  ለመክፈት በእንቅስቃሰሴ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአለም አቀፉ የስነ-ፈለክ ህብረት /IAU/ በአለም ከ10ሺ በላይ አባላት ሲኖሩት፣ ከ230 በላይ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ የሚንቀሳቀስ ህብረት እነደሆነ የገለፁት ደግሞ ዋና ፀሃፊ የሆኑት ፒዬሮ ቤንቬኑቲ ናቸው፡፡ ህብረቱ የህዋ ምርምር ውጤቶችን ለመላው የሰው ልጆች ለማዳረስ እንደሚንቀሳቀሱም ነው የጠቆሙት፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ፣ የትምህርት ሚንስቴር፣ የአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲም ከኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ጋር የስምምነቱ አካል ሆነዋል፡፡