የከተራ በዓል በድምቀት ተከብሮ ዋለ

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2006  (ዋኢማ) – የኢየሱስ ክርስቶስ የበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የከተራ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሮ ዋለ፡፡

በዓሉ በተለይ እዚህ በአዲስ አበባ በሚገኘው ጃንሜዳ የተከበረው በሺህዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች፣የውጭ አገራት ቱሪስቶች፣

አምባሳደሮችና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት ነበር።

ታቦታቱ ከየአድባራቱ ሲነሱ ብዑዓን ጳጳሳት፣የሰንበት ተማሪዎች፣ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ዲያቆናት ቀሳውስት፣

በሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን፣የውጭ ዜጎች በዓሉ ወደሚከበርበት ሥፍራ በታላቅ ድምቀት አምርተዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ  ከብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ወደ ባህረ ጥምቀቱ ሥፍራ ሲደርሱ በበዓሉ አከባበር ላይ በነበሩ ምእመናን ዘንድ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ብጹእነታቸው ቃለ-ምእዳንና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ታቦታቱ ለማደሪያ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳኖቻቸው ገብተዋል፡፡

በነገው እለት ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የጥምቀት በዓል ይከበራል፡፡

በአዲስ አበባ 16 የተለያዩ ቦታዎች የሚያድሩት ታቦታቱ በነገው እለት ከጥቂቱ በስተቀር  በመጡበት አኳኋን ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።