በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት 51 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ የውጭ ባላሃብቶች ፈቃድ ወስደዋል

አዲስ አበባ ሸ ፣ ጥር 12/2006 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት 51 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ የውጭ ባለሃብቶች በተለያዩ መሰኮች ለመሰማራት ፈቃድ መውሰዳቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ነጋሽ እንዳሉት ባለፉት ሶስት ዓመታት 2 ሺህ 164 የውጭ ባለሃብቶች የፕሮጀክት ፈቃድ ወስደዋል፡፡
ፈቃዱን ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል 133 ኘሮጀክቶች ግንባታ የጀመሩ ሲሆን ፣ 637 ኘሮጀክቶች ደግሞ ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ናቸው፡፡
ሥራ የጀመሩት የውጭ ኘሮጀክቶች ለ26 ሺህ ዜጐች ቋሚና ለ35 ሺህ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯዋል፡፡
ፈቃድ ከተሰጣቸው የውጭ ፕሮጀክቶች ውስጥ 423 በግብርና፣ 888 ፕሮጀክቶች በማኑፋክቸሪንግ እና 855 ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው፡፡
አብዛኛውን ደረጃ ከያዙት ባለሃብቶች ውስጥም የቻይና፣ የሱዳን፣ የሕንድ፣ የቱርክ፣ እና የአሜሪካ ዜግነት የያዙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ሲሆኑ ባስመዘገቡት ካፒታል ደግሞ የቱርክ ፣ የሕንድ ባለሃብቶች የመጀመሪያዎችን ደረጃ መያዛቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ሰላምና መረጋጋት በሀገሪቱ መወለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ የሚጠይቁ የውጭ ባለሃብቶችን ቁጥር እንዳሳደገውም ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡