የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል 80 ሚሊየን ፓውንድ የእንግሊዝ መንግስት ለመለገስ ቃል መግባቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2006/ዋኢማ/ – በሀገሪቱ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል ከ80 ሚሊየን ፓውንድ በላይ የእንግሊዝ መንግስት ለመስጠት ቃል መግባቱን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ባለፉት ሶስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱም ከ21 ሚሊየን በላይ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ገርባ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ከእንግሊዝ መንግስት የተገኘው 80 ሚሊየን ፓውንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱ መጨረሻ በንፁህ መጠጥ ውሃ ዘርፍ እቅዱን ለማሳካት ይረዳዋል።

የእንግሊዝ መንግስት ለመለገስ ቃል የገባውን ገንዘብ ለመስጠት በቅርቡ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።   

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ይበልጥ ለማሳደግም መንግስት ከሚመድበው ገንዘብ በተጨማሪ የውጪ ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ በአጠቃላይ ከ450 ሚሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱ መጨረሻ ላይ የሀገሪቱን አማካኝ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት 98 በመቶ ለማድረስ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

ባለፉት ሶስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመትም ከ21 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ የሀገሪቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 68 ነጥብ 4 በመቶ በአማካኝ መድረሱን ገልፀው፤ በዘንድሮው የ2006 የበጀት ዓመትም ከ15 ሚሊየን በላይ ህዝብን የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በከተማ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሲሆን፤ በገጠር 13 ነጥብ 1 ሚሊየን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል በማለት ገልፀዋል።

ቀደም ባሉት አመታት የነበረው የዋሽ ወይም የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን ተቋማትና ፋሲሊቲዎች ቆጠራ ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልፀው፤ ለሚቀጥለው የዋሽ ፕሮግራም ዝግጅት ተጀምሯል ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።