ሽታን የሚቋቋም አዲስ የእንሰት ተክልን ለማበልጸግ ጥናት ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2006/ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ የአገሪቱ ክፍል እንደ ዋንኛ ምግብ የሚያገለግለው የእንሰት ምርት አሁን ላይ በመላ አገሪቱ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡
ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችም ይህን ተክል በአግባቡ በመንከባከብ የዕለት ምግባቸውን ከመሸፈንም ባለፈ የገቢ ምንጫቸው አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ተክል ላይ እየታየ ያለውን በሽታ ለመቅረፍ የተለያዩ መፍትሔዎች ቢቀመጡም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተቀናጀ ጥናት እና ምርምር ባለመደረጉ ውጤታማ ሳይኮን ቀርቷል፡፡
አሁን ታዲያ በእንሰት ላይ የሚከሰተውን በሽታ መቋቋም የሚችል አዲስ የእንሰት ዝርያ በጥናት ለማግኘት የኢትዮጵያ ግበርና ምርምር ኢንስቲትዮት ከአለም አቀፉ የትሮፒካል ግብርና ኢንስቲትዮት ጋር በመሆን ጥናቱን ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት ምክትል ዳይሬክተር አዱኛ ዋቅጅራ በሽታውን ለመከላከል አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ እየሰራ ቢሆንም በሚፈለገው መጠን በሽታውን መቆጣጠር ባለመቻሉ በጥናት የተደገፈ መፍትሔን ለመሻት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የእንሰት ተክል ለድርቅ የማይበገር እና ለአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል በመሆኑ ተክሉን ከሚያጠቃው በሽታ ሙሉ ለሙሉ ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ዝርያን ለማግኘት ይሰራል፡፡
ፕሮጀክቱ የሚመሩት በአለም አቀፉ የትሮፒካል ግብርና ኢንስቲትዮት የእጽዋት ባዮ ቴክኖሎጂስት ሊና ትሪፓቲ በበኩላቸው በእንሰት ተክል ላይ የሚታየውን በሽታ ለመከላከል በሽታውን መቋቋም የሚችል አዲስ ዝርያ በዘረመል ጥናት ለማበልጸግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢሬቴድ ዘገባ በእንሰት ላይ የሚደረገውን ምርምር የሚያግዝ የ2 ነጥብ 59 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍም ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ተገኝቷል ሲል የዘገበው ሳይንስ ደቨሎፕመንት ኔት ነው፡፡