የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስቆም ግብጽ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እሄዳለሁ ማለቷ ምንም ፋይዳ የለውም – የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ጥር 14/2006 (ዋኢማ) – አልሞኒተር የተባለው ድረ ገፅ የሀገሪቱ የመስኖና ውሀ ሀብት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ካሊድ ዋሲፍ አሉት ብሎ ያወጣው ዘገባ ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት አደጋ ውስጥ የሚጥላት በመሆኑ ግንባታው እንዲቋረጥ ሌሎች አማራጭ የዲፕሎማሲ መንገዶችን መፈለግ ጀምራለች ይላል።   

ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት መውሰድ ግብጽ እንደ አማራጭ ያስቀመጠችው የዲፕሎማሲ መንገድ እንደሆነም ያትታል ።   

በዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ መስመር ለመሄድም ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ህጋዊ መብትንም በመከራከሪያነት ትጠቀማለች ነው ያሉት የግብጽ የመስኖና ውሃ ሀብት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ።   

ለዚህም የ1929 እና የ1959ኙ የቅኝ ግዛት ስምምነት አሁንም በማስረጃነት ቀርቧል።
በኢፌዴሪ ውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ይህ ህግ አዋጭነቱ ያበቃለት ነው ይላሉ ።   

ከምንም በላይ ሁለቱ ፊርማዎች የቅኝ ግዛት ይዘት ያላቸው በመሆኑ ውል ሰጭና ውል ተቀባይ ሰጭን ያካተቱ ባለመሆናቸው ከመሰረታዊ ህጋዊ ስምምነት ውጭ የሆኑ ናቸው ።

ግብጽ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ወስዳው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር አንድ መሰረታዊ ነገር ማሟላት አለባት ነው ያሉት አቶ ፈቅ፤ እሱም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅሟን ሊጎዳ እንደሚችል የሚያሳይ ሳይንሳዊ ማስረጃ ማቅረብ ነው።

ይህን አስመልክቶ ደግሞ የኢትዮጵያም ሆነ የግብጽ ባለሙያዎች የተካተቱበት አለማቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እዚህ አዲስ አበባ የሚገኘው የምስራቅ ናይል የቀጠና ጽህፈት ቤትና አለምባንክም ያጠኑት ጥናት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት በግብጽ የውሃ አቅርቦት ላይ የጎላ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን የሚያሳየው ነው ይላሉ ።   

ስለዚህ ግብጽ ይህንን መንገድ መከተሏ ምንም አይነት ፋይዳ የለውም ነው ያሉት አቶ ፈቅ ።       

ከዚህ አካሄድ ይልቅ ግብጽ በሱዳን ተዘርግቶ የነበረውን ውይይት መቀጠሉ ያዋጣታል ያሉት አቶ ፈቅ፤ ከግብጽ ባለስልጣናት በኩል እየተሰማ ያለው ነገር በተፋሰሱ ሀገራት ዘንድ እምነት የሚያሳጣት ከመሆን የዘለለ ነገር አያመጣምም ብለውናል ።   

ከዚህ ቀደም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት እወስዳለሁ ያለችውም ህጋዊ መሰረት የለውም ፤ ምክንያቱም ሂደቱ ሊከናወን የሚችለው ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ፍርድ ቤቱ ይዳኘን ብላ ስልጣን እስከሰጠች ድረስ ነውና ።   

ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን መንገድ በፍጹም የማትከተለው መሆኑን ነው አቶ ፈቅ የሚናገሩት ።       

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በሀይድሮሎጂ ሞዴሊንግ ላይ እና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ሊመጣ የሚችል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎች ይጠኑ ብሎ የአለማቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ ለማስፈጸም በሱዳን ሀገራቱ ለሶስት ጊዜያት መሰብሰባቸው ይታወሳል ።

ሆኖም ሁለቱን ጥናቶች በሚያጠናው ኮሚቴ ስብጥር ላይና በሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ መግባባት ሳይችሉ ስብሰባው ተበትኗል ።    ይሁን እንጂ ግብጽ ጉዳዩን ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ስለማቅረብ ብዙም ያለችው አልነበረም ነው ያሉን አቶ ፈቅ።
እንደሳቸው የግብጽ ባለስልጣናት እስካሁን ግድቡን አስመልክቶ ካሉ ግልጽ እውነታዎች ውጭ የሚንቀሳቀሱበት ምክንያት የግድቡ መገንባት ባለስልጣናቱ በሀገሪቱ ላይ ተጽእኖ በመፍጠሩ አይደለም ፤ ይልቅስ ፖሊቲካዊ ይዘቱ አመዝኗል ።
ኢትዮጵያ የናይል ውሃን ለተፋሰሱ ሀገራት በፍትሃዊነት የሚያከፋፍል የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍን ከተፋሰሱ ሀገራት ቀድማ አጽድቃለች።
የትብብር ስምምነቱ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ምርጥ ተሞክሮዎችንም የወሰደ ነው።
በአሁን ወቅትም በሌሎች ሰባት ሀገራት የሚጸድቅበት ጊዜ ተቃርቧል ።     ስለሆነም ግብፅ በማያወጣ መንገድ ከመጓዝ ይለቅ ተባብሮ መስራቱ ለቀጣይ ተጠቃሚነት አጋዥ ይሆናል ። (ኤፍ.ቢ.ሲ.)