የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት ረቂቅ አዎጆችን አጸደቀ

አዲስ አበባ ፤ ጥር 14/2006 (ዋኢማ) – የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የቁም እንስሳት ግብይትን ለመቆጣጠር የወጣውን ጨምሮ አራት ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ፡፡ ስድስት ረቂቅ አዋጆችንም ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
ምክር ቤቱ የቁም እንስሳት ግብይት ቁጥጥር፣አለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት የሚገዛባቸውን ደንቦች ለማዋሀድ የወጣውን ስምምነት ፣ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ወረራ ያለመፈፀምና የጋራ መከላከያ ስምምነት እንዲሁም የአለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማእቀፍ ስምምነት ላይ የቀረቡትን የዉሳኔ ሀሳቦች መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡
የንግድ የግብርናና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያዘጋጀው የቁም እንስሳት ግብይት አወጅ ቁጥር 819/2006 ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ግብይትን ለመቆጣጠር እና ለማስቆም የሚረዳ ከመሆኑም በተጨማሪ የቁም እንስሳትን ለአገር ውስጥ እና ለዉጭ ገበያ በተሻለ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡
ምክር ቤቱ የትንባሆ ቁጥጥር ማእቀፍ ስምምነት ረቂቅ አዋጅን ያፀደቀ ሲሆን አዋጁ የትምባሆ ምርቶች አቅርቦትና ፍላጎት እንዲቀንስ በማስተማር እና ግንዛቤ በመፍጠር ለህዝብ ጤና አጠባበቅ ትኩረት የሚሰጥ ነው፡፡
በዚሁ በመደበኛ ስብሰባው ስድስት ረቂቅ አዋጆች ለበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲታዩ ተመርተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጆቹ መንግስት ለሚያደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ የሚሆኑ የብድር ስምምነቶች ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ ለትምህርት ጥራት ማሻሻያ፣ ለመንገድ ስራ እና ለመሬት አያያዝ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ይውላሉ፡፡
ብድሮቹ ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር፣ ከአፍሪካ ልማት ፈንድ፣ ከአረብ ባንክ፣ ከኦፔክ ፈንድ እንዲሁም ከሳውዲ የልማት ፈንድ የተገኙ መሆናቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል፡፡