ዩኒቨርሲቲዎች ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ተመለከተ

ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት በሚሰራው ስራ የከፍተኛት ትምህርት ተቋማት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል አስገነዘበ

ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሴቶች ትምህርት እና አመራር በሚል ርዕስ ከህዳር 5-7፣ 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው  የዉይይት መድረክ ላይ የማዕከሉ ዳይሬክተር አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ ፤ ያለ ሴቶች ተሳትፎ የሃገር ዕድገት ሊፋጠን ስለማይችል በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት መምህራን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል ፡፡

በውይይቱ ላይ በቀረቡት ጥናቶች እንደተመለከተው በማህበረሰቡ ውስጥ “ሴት አትችልም” የሚለውን አመለካከት እስካሁን መስበር አልተቻለም ነው ያሉት ፡፡

ሴቶች ራሳቸውን ከኃላፊነት ማሸሻቸውና በአግባቡ ባለማስተዋወቃቸው ፤እንዲሁም በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እምነት ተጥሎባቸው ኃላፊነት  ስለማይሰጣቸው የሚፈለገውን ያህል ሴት አመራሮች ማፍራት እንዳልቻሉ በጥናቶቹ ተመልክቷል ፡፡

የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል ሐምሌ 19፣ 2008 ዓ.ም. ተቋቁሞ የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ፡፡

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ማዕከሉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት መምህራን ጋር የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ መገለጹን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡