በአገሪቱ የተፈጠሩ ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

በአገሪቱ የተፈጠሩ ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት እያከናወናቸው ካሉ አበረታች ጥረቶች ጎን ለጎን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አሳሰበ።

ጽህፈት ቤቱ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ ይፋ አድርጓል።

ጽህፈት ቤቱ በላከው ሳምንታዊ የአቋ መግለጫው ከኢትዮጵያ ህዝብ 70 በመቶው ወጣት መሆኑን አመልክቶ  ከዚህ ውስጥ  6 ሚሊዮኑ   ስራ ፈላጊዎች መሆናቸውን ገልጿል።

መንግስት ይህን ከግንዛቤ በማስገባት በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

በአንድ አመት ብቻ ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ለአብነት ያነሳው መግለጫው፤ አገሪቱ  ካላት ስራ አጥ ወጣቶች አንጻር አሁንም ብዙ መሰራት እንዳለበት ጠቁሟል።

መንግስት ችግሩን ለመፍታት እያከናወናቸው ካሉ ዘርፈ ብዙ  ተግባራት በተጨማሪ ወጣቶች በአገር ውስጥ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ  ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቋል።

በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት በመፍታት ረገድ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና መምህራን እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

የተከሰቱ ግጭቶችን ከመሰረታቸው መፍታት የሚቻለው ህዝቡ የሰላም ባለቤት መሆኑን ተገንዝቦ ለመፍትሄው መንቀሳቀስ ሲችል ብቻ እንደሆነም ተገልጿል።

አገሪቱን በየጊዜው የሚፈታተናትን  ድርቅ በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ  ግብርና በመፍጠር መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፤ ከዚህ አኳያ ግማሽ የሚሆነውን የአገሪቷን አርሶ አደር የመስኖ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አበራርቷል።

እያንዳንዱ አርሶ አደር በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እሲኪሆን  ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም መንግስት አረጋግጧል።

የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም የኑሮ ውድነት አገሪቱ እሰካሁን ሙሉ ለሙሉ ያልተሻገረቻቸው ፈተናዎች በመሆናቸው በቀጣይ ችግሮቹን ለመቅረፍ  በትኩረት እንደሚሰራም በመግለጫው ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በሽግግር ላይ የምትገኝ አገር እንደመሆኗ በየጊዜው የተለያዩ ተግዳሮቶች  ቢያጋጥማትም፤ በመንግስትና ህዝብ የተቀናጀ ርብርብ ሁሉንም ችግሮች መፍታት አንደሚቻል መግለጫው አትቷል።

የሚፈጠሩ ችግሮች ከስር መሰረታቸው ተፈትተው አገር የምትለማው ሁሉም ህዝብ የላቀ ተሳትፎ ሲደርግ ብቻ እንደሆነም ነው በመግለጫው የተመለከተው።

 

የጽህፈት ቤቱ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

የአገራችንን ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት ሁሉም የድርሻውን ይወጣ!

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት፣ ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ መስከረም 29 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም. ለሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ ያቀረቡት የመንግሥት የ2010 ዓ.ም. ረቂቅ እቅድ ምክር ቤቶቹ  በትናትናው ዕለት ከተወያዩበት በኋላ ጸድቋል፡፡

ይኸውም የምክር ቤቶቹ አባላት ባነሷቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ላይ በኢፌዴሪ  ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠባቸው በኋላ ነበር።

ከውይይቱ ለመረዳት እንደተቻለው አገራችን ኢትዮጵያ በሽግግር ሂደት ላይ የምትገኝ አገር ናት። በሽግግር ላይ እንደሚገኝ ማንኛውም አገርም የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመዋታል።

በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተዋል። አሁንም በድርቅ ከመጠቃት አላመለጥንም። ከጠቅላላ ህዝባችን 70 ከመቶ ያህሉ ወጣቶች በሆኑባት አገራችን  አሁንም ቁጥራቸው ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ይፈልጋሉ።

የኪራይ ሰብሳቢነትን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አበረታች ሥራዎች መጀመራችን ጥሩ ሆኖ ሳለ በዚህ በኩል የህዝባችንን እርካታ ከማግኘት አንጻር ግን ብዙ መስራት ይቀረናል። ከዕለት ተዕለት ኑሮአችን ጋር የተያያዘ የኑሮ ውድነት ጉዳይም ያልተሻገርነው ችግር ሆኖ ቀጥሏል።

እነዚህ ሁሉ ችግሮች ግን የማይፈቱ አይደሉም። ያለፍንበት ተሞክሮም እንደሚያሳየን በህዝብና በመንግስት የተቀናጀ ርብርብ የማይፈታ አንዳችም ችግር የለም።

ድርቅን በራሳችን አቅም የመቋቋም አቅማችንን አጠናክረናል፤ ወደ ኢንዱስትሪ የምናደርገው ሽግግር መልክ ይዟል፤ የግብርና ልማታችን በእድገት ጎዳና ላይ ነው፤ የጤና ሥራችን ስኬትን አስመዝግቧል፤ የህዳሴ ግድባችን ግንባታ በህዝቡ ሁለገብ ተሳትፎ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ሥራን በመፍጠር በስኬት ጉዞ ላይ የሚገኙ ወጣቶቻችን ብዙ ናቸው። ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል። ትልቁ ቁም ነገር ያለው፣ አዳጊ ሁኔታ የፈጠራቸውንና መንግሥት የተቀበላቸውን ችግሮች በውል ተረድቶ በመፍትሄዎቻቸው ላይ ርብርብ ማድረጉ ላይ ነው።

ከዚህ አንጻር በክቡር የኢፌዴሪ  ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተገለጸው፣ መንግሥት በለያቸው ችግሮች ላይ ተመስርቶ በተቀመጡት የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ መረባረብ ይገባናል።

በኦሮሚያ እና በኢትዮ ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና መምህራን እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።

 የግጭቱ ምንጭ የሆኑትን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችም ለማስወገድ የተጀመረውን ትግል ማጠናከርም ይገባል። ግጭቶችን ከመሰረታቸው መፍታት የሚቻለው ህዝባችን የሰላሙ ባለቤት መሆኑን ተገንዝቦ ለውጤቱ ሲንቀሳቀስ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

ከወጣቶች ሥራ ፈጠራ አኳያ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁለት ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላችን እንደታዳጊ ሀገር ሊያመጻደቀን ቢችልም፣ ካለን የወጣት ቁጥር ብዛት አንጻር አሁንም ብዙ መስራት የሚጠይቀን ነው።

በዚህ በኩል በዋነኝነት ወጣቶች ራሳቸው ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ለዘላቂ ልማታቸው ትኩረት በመስጠት ለተመቻቸላቸው የተስተካከለ የህይወት ጎዳና ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሥራን በመናቅና ስደትን በመምረጥ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት መለወጥ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ወላጆች፣ የመንግሥት እና የሌሎች ባለድርሻ አካላትና መላው ህብረተሰብ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው።

በየጊዜው የሚያጋጥመንን የድርቅ አደጋ ከመሰረቱ ለመከላከል የሚቻለው አሁንም የግብርና ልማታችንን ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው። በመሆኑም መንግሥት በቀረጸው ፖሊሲና ስትራቴጂ መሰረት ከዝናብ ጥገኝነት የሚያላቅቀንን  ውሃና መስኖን ማዕከል ያደረገውን የግብርና ስራችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል። 

በዚህ በኩል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአገራችን አርሶና አርብቶ አደሮች የመስኖ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸው የሚያኮራን ቢሆንም እያንዳንዱ አርሶ አደር ተጠቃሚ እስኪሆን ድረስ እንቅልፍ ሊኖረን አይገባም።

የግብርና ምርቶቻችንንም እየገነባናቸው ካሉ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ጋር ለማስተሳሰር የጀመርነውን ጥረት ማጠናከር ይገባናል።

እንደነዚህ ዓይነቶቹን ትላልቅ የልማት እቅዶች ስናሳካ ነው በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምንችለው፤ አሁን እያጋጠመን ያለውን የኑሮ ውድነት ፈተናም በዘላቂነት መሻገር የምንችለው።

በአጠቃላይ መንግሥት እነዚህንና የመሳሰሉ ጥሩ ጥሩ የችግር መውጫ መንገዶችን ስላበጀልን ብቻ መፍትሄ ሊሆነን አይችልም። ከመንግሥት ጥረት ጎን የሁላችንንም በባለቤትነት መንፈስ መረባረብ የሚጠይቅ ነው።

 እስካሁን ከመጣንበት ሂደት በተግባር የተማርነውም፣ ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ የምንፈታውና አገር የምትለማው በልማት ሥራዎቻችን ላይ ህዝቦቻችን የላቀ ተሳትፎ ሲኖራቸው ብቻ ነውና!(ኢዜአ)

 

 

2958