የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት በመጭው ማክሰኞ በካርቱም ጉብኝት ለማድረግ እንደሚጓዙ ተገለጸ

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ፕሬዚደንት ሳልቫኪር በመጪው ማክሰኞ ወደ ካርቱም እንደሚያቀኑ ተገለጸ ።          

የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብርን ለማጠናከር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ከሱዳኑ አቻቸው ኦማር ሀሰን አል በሽር ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ ምክክር እንደሚያደርጉ የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢብራሂም ጋንዱር ተናግረዋል፡፡

ሳልዛኪር በሱዳን ካርቱም ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት አል በሽር ጋር በሚኖራቸው ውይይት የጋራ ጥቅሞች ቅድሚያ እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡

የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢብራሂም ጋንዱር ስለማክሰኞው የሳልዛኪር የካርቱም ጉብኝት ሲያብራሩ  የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት  የልማት ድርጅት ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ቅድሚያ የተሠጠው የውይይት አጀንዳ መሆኑን አብራርተዋል፡፡.

በሁለቱ ሀገራት መሀከል በፈረንጆቹ መስከረም 2012 የተፈረመውና ተፈጻሚነቱ የተደነቃቀፈው የትብብር ስምምነት እንዴት መስመር ይያዝ የሚለው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡

ስምምነቱ ተግባራዊ ያልሆነው በድንበር ማዋሰንና በአብዬ ግዛት ጉዳይ ከስምምነት መድረስ ተስኗቸው ነው፡፡ በዚህኛው ውይይታቸው ግን ከስምምነት እንደሚደርሱ ተስፋ መደረጉን ሚንስትር ኢብራሂም ጋንዱር ተናግረዋል፡፡  እኤአ  በ2011 ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተለይታ ራሷን ችላ የዓለም ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የገባችበት ዓመት ነው፡፡

እኤአ በ2013 ታህሳስ ወር ደስታዋን ሳታጣጥም ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገብታ እስከዛሬም ዓለም ስለደቡብ ሱዳን ሰላም እየመከረ ይገኛል፡፡ በዚህ መሃል የሚደርስላቸው ያጡ በሺህ የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ሲሞቱ ቁጥራቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹኋን ደግሞ ለነብሳቸው ሸሽተው ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ተሰደዋል፡፡.

የጦርነቱ ተዋንያን እኤአ በ2015 ላይ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የልማት ድርጅት ኢጋድ ሱዳንን ጨምሮ አባል ሀገራቱ ባደረጉት ጥረት ከስምምነት እንዲደርሱ በማግባባትና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈራረሙ አድርገዋል ፡፡

ከስምምነት ቢደርሱም ግን ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ የፊታችን ሰኔ ወር ላይ ዘለቄታ ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ኢጋድ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ታላቅ የምክክር መድረክ ለማካሄድ ከውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡

የማክሰኞው የፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የካርቱም ጉብኝት ሐምሌ ላይ ከፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አል በሽር የቀረበውን ግብዣ ተከትሎ መሆኑን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡