አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከደኢህዴን ሊቀመንበርነት በፈቃዳቸው ለቀቁ

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሊቀ መንበርነት በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ ።

አቶ ሽፈራው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ስብሰባ ነው  የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን አቅርበው ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸዋል ።

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ  ከደኢህዴን ሊቀ መንበርነትና ሥራ አስፈጻሚነት የሚለቁ መሆኑም  ተገልጿል።

አቶ ሽፈራው ከድርጅቱ ሊቀ መንበርነት ተነስተው  የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንደሚቀጥሉ  መሆኑን  አስታውቀዋል ።

የድርጅቱ ቀጣይ ሊቀ መንበር አሁን በመካሄድ ባለው አስቸኳይ ስብሰባ ወይም ከመጪው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመረጥ ነው ያስታወቁት።

አቶ ሽፈራው በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን መሰረታዊ የለውጥ ሂደት በመደገፍና፥ ለውጡን የሚመራ አዲስ አመራር የሚያስፈልግ በመሆኑ ለውጡ በአዲስ አመራር እንዲቀጥል መፈለጋቸውን  ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች ከአስተዳደራዊ መዋቅር አልፎ ወደ ህዝብ በመግባቱና መፍትሄ የሚያስፈልገው በመሆኑ፥ እንዲሁም ይህ ችግር በእርሳቸው የአመራርነት ዘመን በመፈጠሩ ከዚህ በኋላ በሊቀ መንበርነት የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸውም ገልጸዋል።

አመራር በመቀየር ብቻ ለውጥ አይመጣም ያሉት አቶ ሽፈራው የማይነኩ የተባሉ ጥያቄዎችን መልስ በመስጠት ችግሮችን መፍታት ይገባልም ብለዋል።

በዚህም በአዲስ ጉልበት የሚመጣው አመራር ስራዎቹን እንዲያከናውን ከሃላፊነት ለመልቀቅ መወሰናቸውንም አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ፥ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት አካባቢዎቹን ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ በሚቻልበት አግባብ ላይ እየመከረ ነው።(ኤፍቢሲ)