ከጉጂና ጌድዮ ዞኖች አዋሳኝ ድንበር የተፈናቀሉ ዜጎች ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እጥረት እንዳጋጠማቸው ገለጹ

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን አዋሳኝ ድንበር ላይ በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ  በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ  ዜጎች  ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ እጥረት እንዳጋጠማቸው ለዋልታ ገለጹ ፡፡

ተፈናቃዮችም በጌዲኦ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተጠልለው የሚገኙ ቢሆንም ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ እጥረት እየገጠማቸው በመሆኑ አፋጣኝ  እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል ፡፡

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ከሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ጋር በመሆን አስቸኳይ እና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሠጥም ጠይቀዋል፡፡

በዚሁም በአካባቢያቸው ሰላም የሚሰፍን ከሆነ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ አክለውም መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ የወደሙ ንብረቶቻቸው እንዲመለሱ እንዲሁም የግጭቱ ተዋናይ የሆኑ ዜጎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

በግጭቱም ከ6 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ የሰው ህይወትም ጠፍተዋል ንብረትም ወድመዋል ነው የተባለው፡፡

የጌድኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ ለተፈናቃዮች እየቀረበ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ የተነሳ ዜጎች መቸገራቸውን በመግለጽ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ምላሽና መልሶ ማቋቋም ባለሙያ አቶ ታዬ ጌታቸው በበኩላቸው የፈደራል መንግስት ለተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸው ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተጠናከረ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡