የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም ስነ ሥርዓት አዋጅ ፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም ስነ ስርዓት አዋጅን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የምህረት አሠጣጥና አፈጻጸም ስነ ሥርዓት አዋጅን ከተወያየ በኋላ አፅድቆታል።

አዋጁ ህገ መንግስታዊ ይዘት ያለው ሆኖ በአብዛኛው የፖለቲካ ጥፋቶችን፣ ሀገር መክዳት፣ የአመጽ ወንጀሎችንና በሀገርና በመንግስት ላይ አመፅ ማነሳሳት ወንጀል ለፈፀሙ እና በህግ በተሠጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰው የመንግስትን ህግ እና ሥርዓት ለማክበር ግዴታ ለሚገቡ ጥቂት ወይም መላው ወንጀለኞች መንግስትያለፈውን ወንጀላቸውን ሙሉ በሙሉ ይቅርታ የሚያደርግበት ሥርዓት ነው።

ምህረት መብት ሳይሆን የሀገርን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በተወሰኑ የወንጀል አይነቶች እና በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወይም ወንጀለኞች ላይ ምርመራ ወይም የክስ ሂደት ከማስቀጠል ወይም ቅጣትን ከማስፈፀም ይልቅ ምህረት የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ሲታሰብ የሚሰጥ መሆኑም በአዋጁ ተደንግጓል።

አዋጁ ምህረት ለመሥጠት ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ሁኔታዎችን በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፥ እነዚህም

1. የወንጀል ድርጊቱ በሀገር ሉአላዊነት ላይ የሚያስከትለው ወይም ያስከተለው ተፅዕኖ

2. ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ የተሻለ አማራጭ ስለመሆኑ

3 ምህረት የሚደረግላቸው ሰዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ የሚያሳዩት ፍላጎት መሆናቸው ተደንግጓል።

በአዋጁ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ የሚኒስትሩ የሆነ እና ለምህረት አሰጣጥ እና አፈጻጸም የሚረዱ መስፈርቶችን የሚያወጣ እና የምህረት ጥያቄ ተቀብሎ የሚመረምር ቦርድ እንደሚቋቋም ተደንግጓል።

የቦርዱ አባላትም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል፣ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፣ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚወከል አንድ ዳኛ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰየሙ ሁለት ሰዎች ናቸው።(ኤፍቢሲ)