በኢትዮጵያ እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተፈፀሙ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ

በሀገሪቱ እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተፈፀሙ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣የተቋቋሙት ኮሚቴዎች  ለውጦችን  ለማደናቀፍ እየተፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራትንና ሴራዎችን በማጣራት ለህግ የሚያቀርብ መሆኑንም አስታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ለመደገፍ ህዝቡ ሰኔ 16 ቀን ፤ 2010 ቀን ሰላማዊ  ሰልፍ መውጣቱን የጠቆመው መግለጫው በወጣው ህዝብ ላይ ቦምብ በመወርወር ሂደቱ እንዲስተጓጎልም ተደርጓል ብሏል።

ሰላማዊ ሰልፉን ለማደናቀፍ ቦምብ ከመወርወር ጀምሮ ሂደቱ እንዲስተጓጎል በወቅቱ መብራት እንዲጠፋ እና የቴሌኮም ኔትወርክ የማቋረጥ ተግባር መከናወኑን ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።

በተጨማሪም የኢኮኖሚ አሻጥር በተደራጀ አኳኋን በመስራት የኑሮ ውድነትን እንዲባባስና የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙ ተቋማት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እየተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉንም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።

እንደ አዲስ የተቋቋሙ ኮሚቴዎችም እነዚህን ህገወጥ ተግባራት አጣርቶ ለህግ ለማቅረብ ከተለያዩ አካላት ጋር የተለያዩ ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

ለተልዕኮው ስኬታማነትም መላው ሰላም ወዳድ ህዝብ ከኮሚቴው ጎን በመቆም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግና አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እንዲተባበር ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።

የማጣራት እና የምርመራ ውጤቱም ለህዝብ ይፋ የሚደረግ መሆኑንም አስታውቋል።