በባህርዳር ከተማ የተለያዩ መልዕክቶች የተላለፉበት ሰልፍ ተካሄደ

በባህርዳር ከተማ ትናንት በተካሄደውና የተለያዩ መልዕክቶች የተላለፉበት ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ።

በሰልፉ ላይም ከወልቃይትና ከራያ ማንነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ የሰልፉ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።

ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አቶ መላኩ ቦጋለ እንደገለጹት የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ በማንነት የመብት ጥያቄ ምክንያት የሚደርስ በደል እንዲቆምና ችግሩ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኝ ለመጠየቅ ነው።

የጣና ሃይቅ በእምቦጭ ምክንያት የተጋረጠበተን የመድረቅ አደጋና በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ በፌዴራል መንግስቱ ትኩረት እንዲሰጠው ለማሳሰብ መሆኑንም ተናግረዋል።

መነሻውን ፓፒረስ ሆቴል መዳረሻውን ርዕሰ መስተዳደር ጽፈት ቤት ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ከተላለፉ መፈክሮች መካከልም ከወልቃይትና ከራያ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ጨምሮ ፣ጣና ይፈወስ፣ ላሊበላ ይታደስና ሌሎችም መልዕክቶች ተላልፈውበታል።

የባህር ዳር ከተማ  አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ሰላማዊ ሰልፉ  በሰላም እንዲጠናቀቅ ህዝቡ የራሱን ጸጥታ በማስከበርና በራሱ እየመራ ማስኬዱን አመስግነዋል።

የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችም ሆኑ የጣና ሃይቅና ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አግኝተው መፍትሄ እንዲሰጣቸው የከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ሽማግሌዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።

ተመሳሳይ ይዘትና ዓላማ ያላቸው ሰልፎች በክልሉ በደሴ፣ደብረ ብርሃን፣ሰቆጣና ወልዲያ በዛሬው እለት ተካሒደዋል።

የማንነት ጥያቄዎች የሚነሱባቸው አካባቢዎች ለክልሉ ቀርበው ምላሽ የሚሰጥባቸው ሲሆን በዚህ ያልረካ አካል ስርዓቱን ጠብቆ ለኢፌዴሪ የፌዴርሽን ምክር ቤት ማቅረብ ምላሽ ማግኘት እንደሚችል ይታወቃል።

በዛሬው ሰልፍ ላይ የተነሱ የማንነትና የመብት ጥያቄዎች የቀረበባቸው አካባቢዎችም በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስር የሚተዳደሩ ናቸው።(ኢዜአ)