የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 4ኛ የወንጀል ውሎው ፖሊስ በእነ አብዲ ኡመርና ሌሎች የሶማሌ ክልል የሥራ ኃላፊዎች ክስ መዝግብ ላይ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ፈቅዷል ።
በሶማሌ ክልል ከሐምሌ 26 እስከ 30 2010 ድረስ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት በግለሰቦች ንብረት 741 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ተጠርጣሪዎች እንዲወድም ማድረጋቸውን ፖሊስ መረጃዎችን ማጠናከሩን በችሎቱ ገልጿል ።
የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን በሶማሌ ክልል በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሰዎችን የቃል ምስክርነት ተቀብሏል ።
በተጨማሪም ከተጠርጣሪዎች ጋር በተያያዘ የተገኙ የጽሑፍ መረጃዎች ከሶማሌኛ ወደ አማርኛ እንዲተረጎሙ ማድረጉን ፖሊስ ገልጿል ።
መርማሪ ፖሊስ አጠቃላይ የምርመራ ውጤቶች ለመጠበቅ ፣የቀሩ ሥራዎችን ለማከናወን ፣ የምስክር ቃል ለመቀበል ፣ የወንጀል ግብር አበሮችን ለመያዝና የአስከሬን ምርመራ ውጤትን ለማመሳከር ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲሠጠው ፍርድ ቤቱ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል ።