የሜጀር ጄነራል ኃይሌ ጥላሁን የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ 

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 9/2008 (ዋኢማ) – በሱዳን አቢዬ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ልዑክ መሪ  የነበሩት ሜጀር ጄነራል ኃይሌ ጥላሁን የቀብር ሥነ-ሥርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ትናንት ተፈጸመ።

የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮሰ አድሃኖም እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በስርአተ ቀብራቸው ላይ ተገኝተዋል።

ሜጀር ጄነራል ኃይሌ ጥላሁን በሠላም ማስከበር ሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት ባጋጠማቸው ህመም በውጭና በአገር ውስጥ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ62 ዓመታቸው ነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውም  በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈጽሟል።

ጥር 5 ቀን 1946 ዓ.ም ከወይዘሮ አሰገደች ገብሬ እና ከአቶ ጥላሁን ገብረማርያም በሆሳዕና ከተማ የተወለዱት ሜጀር ጄነራል ኃይሌ ዕድገታቸው ደብረብርሃን ነበር።

የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዘርዓ ያዕቆብ እና በኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ተምረዋል፤ከኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ደግሞ በ1965 ዓ.ም በመምህርነት ተመርቀዋል።

ከእንግሊዝ ኦፕን ዩኒቨርሲቲም በቢዝነስ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ሜጀር ጄኔራል ኃይሌ ጥላሁን ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ወረሂመኖ ተንታ ለሦስት ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1969 ወደ ሰሜን ወሎ ቆቦ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመዘዋወር አስተምረዋል።

በዚሁ ዓመት በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የኢሕአፓ አባል በመሆን የነቃ ተሳትፎ ያደርጉ ስለነበር በደርግ መንግሥት በመፈለጋቸው አምልጠው የኢሕአፓ ሠራዊት ወደ ነበረበት አሲንባ በመሄድ የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅለዋል።

ድርጅቱ እስከ ነበረበት ጊዜ በሠራዊቱ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አመራር ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን የቀድሞውን ኢህዴን የዛሬውን ብአዴን ከመሰረቱት መካከል መሆናቸውንም የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

በድርጅቱ በማዕከላዊ ኮሚቴና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ከፍተኛ አመራር ሆነው አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሲመሰረትም የምክር ቤትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው እስከ 1983 ዓ.ም በአመራርነት ሰርተዋል።

የደርግን መንግሥት ለመገርሰስ ኢህዴን/ኢሕአዴግ ባደረጉት የትጥቅ ትግል በተለያዩ አውደ ውጊያዎች በተዋጊነትና አዋጊነት የተሳተፉ ሲሆን በአሰልጣኝነትና በፖለቲካ መሪነትም ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

ከደርግ ውድቀት በኋላ የአገር መከላከያ ሰራዊት በአዲስ መልክ ሲደራጅም በከፍተኛ መኮነንነት መንግሥትና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ በታማኝነት ፈጽመዋል።

በአገር መከላከያ ሰራዊት በምድር ኃይል አዛዥነት ተመድበው ከአንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ የሚጠበቀውን ተልዕኮ መወጣታቸውንም የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።  

ከሰራዊቱ በጡረታ እስከተሰናበቱበት 1999 ዓ.ም ድረስም የመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናንስና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ በመሆን ለአራት ዓመታት አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት፣በኢትዮጵያ አየር መንገድና በሌሎችም መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች የቦርድ አመራር አባል በመሆንም ሰርተዋል።

በመጨረሻም በሱዳን አቢዬ ግዛት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም አስከባሪ ልዑክ መሪ እና የአቢዬ የበላይ ጠባቂ ሆነው በመሾም ለአንድ ዓመት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል።

ሜጀር ጄኔራል ሀይሌ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።