የአሸንዳ፣ አሸንድዬ እና ሻደይ በዓላት እየተከበሩ ናቸው

የአሸንዳ፣ የአሸንድዬ እና ሻደይ በዓላት ትግራይ እና በአማራ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከበሩ ናቸው ።

በዓላቱ በተለይም በመቐለ አሸንዳ፣ በላሊበላ አሸንድዬ  እና በሰቆጣ ሻደይ በመባል ነው በድምቀት እየተከበሩ ያሉት።

በራያ ቆቦ አካባቢም ሶለል በሚል መጠሪያ በዓሉ እየተከበረ ይገኛል።

በዓላቱ በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል የሚከናወኑ የልጃገረዶች የአደባባይ ክብረ በዓላት ናቸው።

ወጣቶች ተያይተው በሚተጫጩበት የአሸንዳ፣ አሸንድዬ እና ሻደይ በዓላት ላይ ለመሳተፍ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የውጭ እና የሀገር ውስጥ እንግዶች መቐለ፣ ላሊበላ እና ሰቆጣ ከተማ ገብተዋል። 

በሴቶች የሚደምቁት እነዚህ ህዝባዊ በዓላት ፀጉር አሠራራቸው በትግራይ አልባሶ፣ ግልብጭ፣ ከጋመ፣ ድርብ ሲባል በሰቆጣና በላሊበላ አካባቢ ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ግልብጭ፣ ሳዱላና ቅርድድ የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ 

ልጃገረዶቹ ለበዓሉ ድምቀት የሚጠቀሟቸው ጌጣጌጣጦች ሕንቆ፣ አልቦ፣ ድሪ፣ ድኮት፣ ጉትቻ፣ ማርዳ፣ መስቀል ሲሆን፥ አለባበሳቸውም በመልጉም /ጥልፍ ቀሚስ/፣ ሹፎን፣ ጃርሲ የታጀበ ነው፡፡ 

በዓላቱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

በተያያዘ የአሸንዳ በዓል በአዲስ አበባ ነሐሴ 28 እንደሚከበር የትግራይ ሴቶች ማህበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቋል።

በዓሉ "ባህላችንን በማበልጸግ ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበር ይሆናል።

የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ምህረት ምናስብ፥ “በዓሉ ለሴቶች የነጻነትና የማንነታቸው መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር አንድነትን የሚያጠናክር በዓል ነው” ብለዋል።

በመሆኑም በዓሉን ጠብቀንና ተንከባክበን ለቀጣይ ትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል ነው ያሉት።

በዓሉን ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በድምቀት ማክበር የሚያስችል ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም ጠቁመዋል።

በዕለቱ ከ20 ሺህ በላይ ታዳሚዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዕለቱ ከመግቢያ ትኬት ሽያጭና ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን እስካሁን 20 ሺህ ትኬቶች ተሸጠዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።

ተጨማሪ መረጃ ከኢዜአ