ኮሚሽኑ የረመዳን በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማደረጉን አስታወቀ

የረመዳን በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን የደህንነት ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ እንዳስታወቁት፤ከእምነቱ ተከታዮችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ተዘጋጅተዋል  

በዓሉ አርብ ወይም ቅዳሜ ይከበራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም በፖሊስ ሊደረጉ የሚገቡ የቁጥጥር፣ የፍተሻና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  በቅንጅት ለመስራት በቂ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ለማክበር ወደ እምነት ተቋማት በሚሄድበት ወቅትም የመኖሪያ ቤቱን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ምዕመናኑ ተሰባስበው በሚያከብሩባቸው አካባቢዎች የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችም  መደረጋቸውንም ገልጸዋል

በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ያሉ መተላለፊያ መንገዶች ማለትም ከአራት ኪሎ በቤተ መንግስት ወደ ስታዲዮም የሚወስደው፣ ከሰንጋ ተራ በጥቁር አንበሳ ወደ ብሄራዊና ስታዲየም የሚወስደው፣ ከለገሃር ወደ ሜክሲኮ የሚወስደውና  ሌሎች መስቀል አደባባይን የሚያቋርጡ መንገዶች  በበዓሉ እለት ለትራፊክ ዝግ እንደሚሆኑ ኮማንደር ፋሲካ አስታውቀዋል።

አሽከርርካሪዎች ይህን በመገንዘብ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።

በዓሉን በሰላም ለማክበርም ህዝበ ሙስሊሙና ሌላው ማህበረሰብ ማንኛቸውንም ወንጀል ነክና ለደህንነት አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮችን ለአካባቢው ፖሊስ  በመጠቆም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉም  ጥሪ አቅርበዋል። (ኢዜአ)