ሀገር አቀፉ ፈተና በተያዘለት ፕሮግራም እየተካሄደ እንደሆነ ተገለጸ

የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተያዘለት ፕሮግራም እየተካሄደ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የትምህርት ሚኒስሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ እስካሁን ያለዉ ሂደት መልካም ነዉ፤ ፈተናዉን አስመልከቶ በማህበራዊ ድረገፆች የሚነዙ ሀሰተኛ ወሬዎች ወደ ጎን በመተዉ ተፈታኞች በፈተናዉ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ከፈተናዉ መጀመር አስቀድሞ የፈተና አወጣጥ ሂደቱ ግልፅና ፍትሐዊ እንዲሆን በካሜራም ጭምር የተደገፈ ስራ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ሂደቱ ሰላማዊና የተረጋጋ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ሚኒስቴር ከፊዴራል ፓሊስ፣ ከመከላከያ፣ ከሰላም ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በ2ሺህ 866 የፈተና ጣቢያዎች እና በ138 መስመሮች የፈተና ወረቀቶች ስርጭት በሄሊኮፕተር በመታገዝ ተከናዉኗል ተብሏል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ነጥብ 5ሚልየን በላይ ተማሪዎች ፈተና እንደሚወስዱ ታውቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ45 ሺህ 981 ያህሉ የአዲስ አበባ ተፈታኞች ናቸው፡፡

የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፉ ፈተና ሰኔ 5 ይጠናቀቃል፡፡